ዘንድሮ 100 ሺህ ሄክታር መሬት የቡና ማሳ ላይ ጉንደላ ይካሄዳል

286

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18/2012 (ኢዜአ) ዘንድሮ 100 ሺህ ሄክታር መሬት የቡና ማሳ ላይ ጉንደላ ወይም እደሳ እንደሚካሔድ የቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ።

የቡና ተክል ጉንደላ ማካሄድ ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግና የተሸለ የቡና ምርት ለመምጣት እንደሚያስችልም ተገልጿል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ጉንደላ የቡና ምርታማነትን እንደሚያሳድግ ቡና አምራቾች እየተገነዘቡ መጥተዋል።

''ጉንደላው ምርቱን በመጠንም ሆነ በጥራት ለማሳደግ ከተያዙት ስትራቴጂ መካከል ነው'' ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረውን ቡና በመጎንደል እንዲታደስ ማድረግ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።

ያረጀ የቡና ተክል በሄክታር ሰባት ኩንታል እንደሚገኝበት ያስታወሱት ዶክተር አዱኛ፤ ከጉንደላ በኋላ የቡና ምርታማነት እየጨመረ ስለሚመጣ ምርቱ በሄክታር እስከ 26 ኩንታል እንደሚያድግ ጠቁመዋል።

ለጉንደላው የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን መንግሥት እያቀረበ ሲሆን፤ ሌሎች አካላት ክትትልና ድጋፍ በማድረግ  ባለሙያዎችን እየረዱ መሆናቸውን አንስተዋል።

ጉንደላው የምርቱን ጥራት ለማሳደግና ልዩ ጣዕም ያለው ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ጠቁመዋል።

ባለስልጣኑ ለቡና አምራች አርሶ አደሮች ገበያ የማፈላለግ ስራው ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ጥራት ያለው ቡና ማቅረብ ሲችሉ እንደሆነ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ባለፈው አመት 50 አምራቾች ቡና በቀጥታ ወደውጭ መላክ መቻላቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ዘንድሮ 295 ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት እየሰራች  መሆኗን ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም