የእርቀ ሰላም ኮምሽን ተስፋ ሰጭ ስራዎችን እያከናወነ ነው

143

 አዲስ አበባ የካቲት 18/2012 (ኢዜአ) የእርቀ ሰላም ኮምሽን እያከናወነ ያለው ተግባር ተስፋ ሰጭ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።

አፈጉባኤው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን እያከናወነ ባለው ተግባርና ቀጣይ ስራዎችን በተመለከተ በዛሬው እለት ከኮሚሽኑ አባላት ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅትም የእርቀ ሰላም ኮምሽን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ለህዝቦች ሰላምና አንድነት እያከናወነ ያለው ስራ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን አፈ ጉባዔው ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ እዚህም እዚያም የሚፈጠሩ መቃቃሮች ወደ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲመለሱና እርቅ እንዲፈጠር ማድረጉ የሚያስመሰግነው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

እርቅና ሰላምን ማስጠበቅ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ሆኖ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ተደራሽ ሊሆን ይገባል ያሉት አፈ ጉባኤው ጥንቃቄና ብልሃት የሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ኮምሽኑ በጥንቃቄ እንዲሰራም ጠይቀዋል።

ምክር ቤቱም ኮምሽኑ በሚያስፈልገው ማንኛውም አይነት ድጋፍና እገዛ ከጎኑ መሆኑን አውስተው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ተቋማት፣ የክልል መንግስታትና ርዕሰ መስተዳደሮች፣ የከተማ ከንቲባዎችና ሌሎች የስራ ኃላፊዎችም ከኮምሽኑ ጋር በጥምረት የሚሰሩበትን ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚሰራም አክለዋል።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በዚሁ ውይይት ላይ እንደተናገሩት የኢትዮጵ ህዝብ እርቅና ሰላምን ለማስፈን ጽኑ ፍላጎት አለው።

የኮሚሽኑ አባላት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው ውይይት ባደረጉበት ወቅት ያረጋገጡትም ይህንኑ መሆኑን ገልፀው የህዝቡ አብሮነትና ወዳጅነት ጠንካራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በማንኛውም የእርቅ ጉዳዮች ላይ ከአካባቢው ማህበረሰብ፣ ከክልል መስተዳደሮች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ጋር መስራታቸውን የጠቆሙት ሰብሳቢው ”የኢትዮጵያውያን አብሮ የመኖር እሴት በቀላሉ አይሸረሸርም” ብለዋል።

ከህዝቡ ጋር በሰላምና በአንድነት ዙሪያ የተደረገው ውይይት ስኬታማ እንደነበርም ጠቅሰዋል።

በተለይም ግጭቶችና አለመግባባቶች ተከስተውባቸው በነበሩ አካባቢዎች የተከናወነው የውይይትና እርቅ ስኬታማ ነበር ብለዋል።

ኮሚሽኑ ቀጣይ በሚያከናውናቸው ስራዎች የምክር ቤቱ ድጋፍና እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ኮሚሽኑ በእርቅና ሰላም ዙሪያ የአባላቱን ግንዛቤ ለማሳደግ በኬንያና ደቡብ አፍሪካ የተሞከሮ ልውውጥና ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉንም አድንቀዋል።

የኮሚሽኑን የመረጃ አያያዝ ስርአት ለማዘመን የዳታ ቤዝ አሰራር ለመዘርጋት የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁም ታውቋል።