በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ መቆጣጠር ተቻለ

279

አርባምንጭ ኢዜአ የካቲት 17/2012፡- በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ላይ ዛሬ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉን የፓርኩ ስራ አስኪያጅ አስታወቁ።

ስራ አስኪያጁ  አቶ ሽመልስ ዘነበ ለኢዜአ እንደገለጹት  የእሳት ቃጠሎው የተነሳው ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ በፓርኩ ሰንጎ ሜዳ በሚባለው  ስፍራ  ነው።

በቃጠሎም 40 ሄክታር ያህል የፓርኩ አካል መጎዳቱን ጠቅሰው በዚህም ከኤሊ በስተቀር በሌሎች የዱር እንስሳት ላይ ጉዳት አለመድረሱን አመልክተዋል።

አቶ ሽመልስ የቃጠሎው መንስኤ በጫሞ ሀይቅ ዳርቻ የሚገኙ ህገ-ወጥ አሣ አስጋሪዎችን ጠርጥረዋል፡፡

ሆኖም የቃጠሎው  ከተነሳበት አንድ ሰዓት ቆይታ በኋላ በህብረተሰብ ተሳትፎ በተደረገው ርብርብር መቆጣጠር መቻሉን አስታውቀዋል።

የጋሞ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ሬታ ተክሉ በበኩላቸው እሳቱን ለመቆጣጠር ፖሊስ፣ መከላከያ ሠራዊትና የፓርኩ ጥበቃዎች ወድያውኑ በመሰማራት ድጋፍ ማድረጋቸወን ገልጸዋል።

በቃጠሎው ከፓርኩ ሣሮችና ዛፎች ውጭ በእንስሳት ላይ የከፋ አደጋ ሳያስከትል መግታት  መቻሉን ተናግረዋል።

የአደጋው ን መንስኤ ለማጣራት የዞኑ ፖሊስ እንደሚሠራም ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ዓመትን በተመሳሳይ በዚሁ ወርና ቦታ ላይ የእሳት ቃጠሎ ተነስቶ  ከ600 ሄክታር በላይ የፓርኩ አካል መጉዳቱም ተመልክቷል።