አዲሱ የከተማ መሬት አዋጅ በርካታ ችግሮችን እየፈታ ነው

238

መቐለ /ኢዜአ/የካቲት 18/2012 ዓም አዲሱ የከተማ መሬት አዋጅ ተከትሎ የተዘጋጀው መመሪያ ከመሬት ጋር ተያይዘው ሲታዩ የነበሩ ችግሮች እየቀረፈ መሆኑን የተለያዩ አካላት ገለፁ ።

አዋጁን ተከትሎ የወጡ መመሪያዎች በትግራይ ክልል ተግባራዊ ለማድረግ ከመሬት አገልግሎት ባለሙያዎችና ትላንት ውይይት ተደርጓል።

 መመሪያዎች ከአሁን በፊት በከተማ መሬት ላይ ይታዩ የነበሩ ክፍተቶችን መዝጋቱን ተገልጸዋል።

በትግራይ ንግድ ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አታክልቲ ገብረህይወት እንደገለጹት የመሬት አገልግሎት አሰጣጥ በክልሉ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ቆይቷል።

ከአሁን በፊት በአሰራር ላይ የነበሩትን የግልፅነት ችግሮችና የተደበላለቁ አሰራሮች አዲሱን የመሬት አዋጅ እንዲስተካከሉ አድርጓል ።

 ከአሁን ቀደም በነባር ባለ ይዞታዎች ላይ ፋይላቸው የጠፋባቸው ባለጉዳዮች የባለቤትነት ማረጋገጫም ሆነ ሌሎች አገልግሎቶችን እንዳያገኙ ይከለክል እንደነበር በማሳያነት ጠቅሰዋል።

 በአዲሱ የከተማ መሬት አዋጅ  ግን ይህንኑ አሰራር እንዲየቀር ማድረጉን አቶ አታክልቲ ተናግረዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች የባለቤትነት ማረጋገጫ ፋይል የሌላቸውና የጠፋባቸው ነባር ባለይዞታዎች በስማቸው ግብር የከፈሉበትና ሌላ በእጃቸው የሚገኝ ሰነድ ህጋዊነት እንዲኖረው ማድረጉ ተገቢ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  በእንትጮ ከተማ  የማዘጋጃ ቤት ባለሞያ አቶ ገብረስላሴ በላይ ናቸው።

ፋይል የጠፋባቸው ሰዎች በማዘጋጃ ቤት ፋይል እንዲከፈትላቸውና ማንኛውም አገልግሎት እንዲጠቀሙ አዲሱ አሰራር መፍቀዱ ለአመታት የቆየውን የመልካም አስተዳደር ችግር መቅረፉን  አቶ ገብረስላሴ ተናግረዋል።

በመቐለ ከተማ አስተዳደር  የማዘጋጃ ቤት ባለሞያ አቶ ደስታ ካሕሳይ በበኩላቸው የከተማ መሬት ለሊዝ ጨረታ በሚወጣበት ወቅት ለዋስትና በማስያዣነት ይከፈል የነበረው  5 በመቶ የሊዙ መነሻ ዋጋ እንዲስተካከል መደረጉ አግባብነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

አንድ ግለሰብ የሚጫረተው የከተማ መሬት ብዛት ገደብ ያልነበረው በመሆኑ በከተማ መሬት ላይ ኪራይ ሰብሳቢዎች የበላይነታቸው ይዘው መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በአዲሱ የከተማ መሬት ሊዝ አሰራር ለዋስትና የሚያሲዘው ገንዘብ ከ5 በመቶ ወደ  20 በመቶ ከፍ እንዲል መደረጉ አንድ ሰው በበርካታ ቦታዎች ከመወዳደር ይልቅ በውስን ቦታዎች እንዲወዳደር የሚያስገድድ በመሆኑ ለሌሎች ተወዳዳሪዎች እድል ይሰጣል ብለዋል።

ከአንድ ቦታ በላይ ለሚጫረቱ  ሰዎችም ለዋስትና የሚያስይዙት ገንዘብ በያንዳንዱ የሚጫረቱበት ቦታ ሌላ 5 በመቶ እንዲጨምሩ መደረጉ ፍትሃዊነት የሚያስፍን ከመሆኑም ባሻገር የከተማ መሬትን በውስን ሰዎች እጅ እንዳይገባ ያደርገዋል ብለዋል።

በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የከተሞች ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ሰለሞን ኪዳነ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንደገለጹት የከተማ መሬት በአግባቡ ማስተዳደር ባለመቻሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚታዩበት ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሙሁራን ሰፊ ጥናት ሲያደርግ መቆየቱን የገለጹት አስተባባሪው በአሁኑ ወቅት ከአደረጃጀት ጀምሮ የተለያዩ ማስተካከያዎች እየተደረጉ መሆናቸው አስረድተዋል።

በክልሉ ከተሞች የሚሰሩ ባለሙያዎች ከአዋጅ ጀምሮ እየተደረጉት ያሉትን ለውጦችና አሰራሮች መከታተልና ለተግባራዊነታቸው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

አዲሱ የከተማ መሬት አዋጅ  ባለፈው አመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ተግባር መሸጋገሩን ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም