በትግራይ ለተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ከ40 ሚሊዮን ብር በጀት ተመደበ

179

መቀሌ ኢዜአ የካቲት 18/2012 ዓ/ም በትግራይ በሚገኙ 36 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለተጀመረው የተማሪዎች የምግባ ፕሮግራም ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ። 

በቢሮው  የምገባ ፕሮግራሙ አስተባበሪ አቶ አፅብሃ ሃይለዝጊ ለኢዜአ እንዳሉት ፕሮግራሙ የተጀመረው የምግብ ዋስትና ችግር አለባቸው ተብለው በተለዩ የሀውዜን፤ ክልተኣብላዕሎ እና አፅቢወንበርታ ወረዳዎች ውስጥ ነው።

በወረዳዎቹ ውስጥ ከሁለተኛ የትምህርት መንፈቅ ዓመት ጀምሮ መካሄድ ለጀመረው የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ከ40 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን አስታውቀዋል።

በጀቱን  የተመደበው በክልሉ መንግስት እና  ማሕበር ደናግል ደቂ ፍቅሪ ትግራይ በተባለው ሀገር በቀል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ትብብር መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም እያንዳንዱ ተማሪ በቀን ውለው 600 ግራም  ኃይል ሰጪ ምግብ ለማዳረስ  እንደሚያስችል  አመልክተዋል።

በፕሮግራሙ በ36 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ  24ሺህ 320 ተማሪዎች ተጠቃሚ ሲሆኑ ከመካከላቸውም 14ሺህ በላይ ሴቶች ይገኙበታል።

ይህም በኢኮኖሚያዊ ችግር ምክንያት ከመደበኛ የትምህርት ገበታቸው ይቀሩ የነበሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን  በአግባቡ እንዲከታተሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን  አቶ አፅብሃ አስረድተዋል።

በቀጣዩ መጋቢት ወርም የምግብ እጥረት አለባቸው ተብሎው በተመረጡ የሳዕስዕ ጻእዳእምባ እና ኢሮብ ወረዳዎች በሚገኙ 38 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራሙ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

በምስራቃዊ ዞን አፅቢወንበርታ ወረዳ የሀበስ አንደኛ ደረጃ ትምህርትቤት ርዕሰ መምህር ባህረ ኃይሉ በበኩላቸው፣”የምገባ ፕሮግራሙ ተማሪዎች ለትምህርታቸው ትኩረት እንዲሰጡ እያገዛቸው ነው”ብለዋል።

ልጆቻቸውን በአግባቡ ለመመገብ አቅም የሌላቸው ወላጆችም ችግር ማቃለሉን ተናግረዋል።

በዚሁ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ዘመዳ በርሀ በሰጠችው አስተያየት የፕሮግራሙ መጀመር በወላጆቿ ላይ ይደርስ የነበረው  ጫና መቀነሱንና በዚህ ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች።

ፕሮግራሙ በተለይ ወላጆቻቸውን ላጡ ህጻናት ተማሪዎች እና አነሰተኛ ገቢ ላላቸው ወላጆች ትልቅ እፎይታን መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ በምስራቃዊ ዞን ክልተአውላዕሎ ወረዳ የበዓቲ ዓኾር ቀበሌ ነዋሪና በፕሮግራሙ በምግብ ዝግጅት የስራ እድል ያገኙ እናት ወይዘሮ ስላስ ፀሃዩ ናቸው።

“ምግብ በማዘጋጀትና በማቅረብ ተግባር ለተሰማራን እናቶችም የሥራ እድል ፈጥሮልናል “ያሉት ወይዘሯዋ፣በየወሩ 800 ብር ደመወዝ  እንደሚከፈላቸው ተናገረዋል።