ጉራጌ ለሚታወቅበት ስራ ወዳድነት መጠናከር እንሰራለን...የወልቂጤ ከተማ የሃገር ሽማግሌዎች

153
ወልቂጤ ሰኔ 21/2010 ወጣቶች የጉራጌ ብሔረሰብ የሚታወቅበትን የስራ ወዳድነት ባህል በማጠናከር በአንድነትና በፍቅር በሃገሪቱ ለውጥ ላይ እንዲሳተፍ እንደሚያደርጉ የወልቂጤ ከተማ የሃገር ሽማግሌዎች ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ እየታየ ላለው ለውጥ የድጋፍና የምስጋና ሰልፍ በወልቂጤ ተካሄደ፡፡ በሰልፉ የተገኙት የሃገር ሽማግሌዎች በጋራ ባስተላለፉት መልእክት ጉራጌ ወደሚታወቅበት የስራ ወዳድነት ባህሉ እንዲመለስ፣አንድነትና ፍቅሩ እንዲጠናከር ከወጣቶቹ ጋር በጋራ እንሰራለን ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በወልቂጤ ከተማ ተገኝተው ለጉራጌ ዘርማዎች ጉራጌ ሁኑ ብለው ያስተላለፉትን መልእክት ተከትሎ ወጣቶች ለጠየቁት ይቅርታም ምስጋናቸውን ቸረዋል፡፡ "በሃገሪቱ እየታየ ላለው ለውጥ አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስቴር የሚያስመሰግን ነው" ያሉት የሃገር ሽማግሌዎቹ የነዳጅ መገኘትን ዜና ሲሰሙ መደሰታቸውንም ጠቁመዋል። በአዲስ አበባ የደረሰው የቦምብ ጥቃት ኢትዮጵያዊነትን የማይወክል በመሆኑ እንደሚያወግዙትም ተናግረዋል፡፡ "ለውጥን እንደግፍ ዴሞክራሲን እናበርታ" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ሰልፍ ከዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ታዳሚዎች ተገኝተዋል፡፡ የሰልፉ አስተባባሪና የጉራጌ ዘርማዎች ተወካይ ወጣት ዳውድ ካሚል በሰልፉ ላይ እንደገለጸው የዘርማ ጥያቄ ለህዝብ አንድነት ሰላምና ልማት መረጋገጥ በመሆኑ ለመብትና ነጻነታችን ተደምረን እንታገላለን ብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጭር ጊዜ በሃገሪቱ እያሳዩት ያለውን ለውጥ ለመደገፍ በአዲስ አበባ በተካሄደ ሰልፍ ላይ የደረሰው የቦምብ ፍንዳታ በኢትዮጵያዊያን ላይ የተቃጣ በመሆኑ እንደሚያወግዙት ተናግሯል፡፡ ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል የጉራጌ ዘርማዎች አባል የሆነችው ልደት ተክሌ "የድጋፍ ሰልፉ የተሳካና ሁሉንም በአንድ ሃሳብ የደመረ ነው" ብላለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወልቂጤ ላይ ተገኝተው የሰጧቸውን ተልእኮ በፍጥነት በማሳካታቸው ደስተኛ መሆኗን ገልጻ "ተደምረን በለውጥ ሂደቱ ሃላፊነታችንን እንወጣለን" ብላለች። በአዲስ አበባ በቦምብ ፍንዳታ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎችም ከጓደኞቿ ጋር የደም ልገሳ ማድረጓን ተናግራለች። በሰልፉ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የተገኙ ሲሆን ድጋፋቸውን የሚገልጹ የተለያዩ መልዕክቶችን የያዙ መፈክሮችን አሰምተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሚሆን የደም ልገሳ ፕሮግራም ተካሂዶ ሰልፉ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተጠናቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም