በ50 ሚሊዮን ዶላር የመጠጥ ውሃና የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ ሊካሔድ ነው

131

ድሬዳዋ የካቲት 17/2012 (ኢዜአ) በሀገር አቀፍ ደረጃ በ50 ሚሊዮን ዶላር በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የንፁሁ መጠጥ ውሃና የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማካሔድ መታቀዱን የውሃና መስኖ ኢነርጂ ሚኒስቴር ተናገሩ ፡፡

በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ይፋ የተደረገበት ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ ዛሬ በድሬዳዋ ተካሔዷል፡፡

በውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ፕሮጀክቶች አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ጋሼ ከውይይቱ በኋላ ለኢዜአ እንደተናገሩት  በሚቀጥሉት 5 ዓመታት በመላው ሀገሪቱ በ22 ወረዳዎች በሚገኙ 66 የገጠር ቀበሌዎች በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የንጹሁ መጠጥ ውሃና የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ይካሔዳል ።

ቀበሌዎቹ የከፋ የንፁሁ መጠጥ ውሃ ችግር ያለባቸውና ለአየር ንብረት ለውጥ የተጋለጡ በመሆናቸው ቅድሚያ እድል እንዲያገኙ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ በግሪን ክላይሜንት ፈንድ ፕሮጀክት 45 ሚሊዮን ዶላር በመንግስት ደግሞ 5 ሚሊዮን ዶላር በጀት መመደቡን ተናግረዋል ፡፡

ፕሮጀክቶቹ ከ3 መቶ ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ አንደሚያደርጉ አቶ ወርቅነህ ገልፀዋል ።

እቅዱ የቀበሌዎቹ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ሽፋን ወደ 80 በመቶ ከፍ የሚያደርገው ሲሆን በመስኖ ልማት ደግሞ ከ5 ሺህ 4 መቶ ሔክታር መሬት  በማልማት የነዋሪውን ኑሮ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሻሽለው አስረድተዋል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር የግብርና ፣ ውሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው የተገኘውን በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ በማዋል በድህነት ውስጥ የሚገኘውን ህብረተሰብ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ  በቁርጠኝነት መስራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡን የሚጠቅም በመሆኑ ፕሮጀክቶቹን በቁርጠኝነት እንተገብራለን ያሉት ደግሞ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ውሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ኃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋሹ ዱጋዝ ናቸው፡፡

በአፋር ክልል የውሃ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ የኢነርጂ ዳይሬክተር አቶ ያሲን አንፉሬ በበኩላቸው የሚተገበሩት ፕሮጀክቶች ታዳሽ ኃይል ላይ ያተኮሩ በመሆናቸው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ በአግባቡ ለማቋቋም ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል ።

የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በ35 ሚሊዮን ብር በድሬዳዋ ለገኦዳ ጉኑን ፈታ ገጠር ቀበሌ የተገነባውንና በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የንጹሁ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ጎብኝተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም