የኦሎምፒክ ድሎች በሁሉም መስክ ለመድገም መረባረብ ያስፈልጋል

79

ድሬዳዋ፣ የካቲት 17/2012 (ኢዜአ) በኦሎምፒክ አደባባይ በተደጋጋሚ ጊዜ የተመዘገቡ ድሎች በሁሉም መስክ ለመድገም አንድነታችንን አጠናክረን መረባረብ አለብን ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ገለፁ ፡፡

የቶኪዮ 2020 የሀገራችንን ተሣትፎ የሚያበስረው የኦሎምፒክ ችቦ በድሬዳዋ ደማቅ አቀባበልና አሸኛኘት ተደርጎለታል፡፡

ሠላም ፣ ፍቅርና አንድነትን ለማፅናት ፤ በስፖርቱ ላይ የህዝብ ንቅናቄ ለመፍጠርና ገቢ ለማሰባሰብ በዋና ዋና የሀገሪቱ ክልሎችና ከተሞች የኦሎምፒክ ችቦ እየተጓጓዘ ይገኛል፡፡

ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ችቦው ዛሬ ድሬዳዋ በገባበት ወቅት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የድሬዳዋ ነዋሪዎችና አመራሮች ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል ።

በሥነ- ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና የኦሎምፒክ ብሔራዊ ኮሚቴ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ በስነ ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራችንን ወደ ብልፅግናና ዕድገት ለማሸጋገር ሁሉም ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

የሀገራችን ህዝብ በኦሎምፒክ መድረክ የሚፈጥረውን ህብረትና አንድነት በሁሉም መስክ ለመድገም ሊረባረብ እንደሚገባም ምክትል ከንቲባው አሳስበዋል ።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ በበኩላቸው ሀገራችንን በሁሉም የስፖርት መስኮች በኦሎምፒክ አደባባይ ስሟን የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን ለማፍራት የተቀናጀ ጠንካራ ሥራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስፖርት ያለመንጠፍ አብቦ በትውልድ ቅብብሎሽ እንዲጓዝ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሥራው 3 ቢሊዮን ብር መመደባቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህም ስፖርቱን የሚያግዝ በፌደራል ደረጃ ትልቅ የኦሎምፒክ መንደር ለመገንባት ያስችላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው ሀገራችን በስፖርቱም ሆነ በሁሉም መስክ ከብልጽግና ወደ ብልጽግና ለማሸጋገር የጀመርነውን ጉዞ  በፍቅር፣ በአንድነትና በመደመር መንፈስ እጅ ለእጅ ተያይዘን መስራት ይገባናል ብለዋል፡፡

የኦሎምፒክ ችቦ በድሬዳዋ ቆይታ ካደረገ በኋላ ቀጣዩ ጉዞውን ወደ ሶማሌ ክልል ጅጅጋ አቅንቷል፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተሣተፉት የድሬዳዋ ነዋሪዎች ሀገራችን በኦሎምፒክ መድረክ የለመደችውን ውጤት እንድታስመዘግብ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም