በክልሉ በ15 ሚሊየን ብር የተገነቡ የትምህርት ማስፋፊያ ህንፃዎች ተመረቁ

65

ሐረር  የካቲት 17/2012 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል 15 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ የተገነቡ የትምህርት ቤት ማስፋፍያ ህንጻዎች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ።

በክልሉ የትምህርት ፍትሃዊነትና ተደራሽነት ለማጎልበት የክልሉ መንግስት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ገልጸዋል።

ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት የበቁት የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች በከተማው ጀግኖች መታሰቢያ  ራስ መኮንን አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የተገነቡ መሆናቸውን በምረቃው ወቅት የተናገሩት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ ናቸው።

ህንፃዎቹ ለቢሮ ፣ ለመማሪያ ፣ ለአይ ሲ ቲ፣ ለቤተ ሙከራና ቤተ መጽሃፍት የሚያገለግሉ 60 ክፍሎች መያዛቸውንና ለማስተማሪያ የሚያገለግል ሙሉ ቁሳቁስ እንደተሟላላቸው ገልጸዋል።

ህንጻዎቹ ከ400 በላይ ተጨማሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ እንደሚያስችሉም አቶ ሙክታር አክለው ተናግረዋል።

በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ባደረጉት ንግግር የአካባቢው ህብረተሰብ ለረዥም ጊዜ ሲጠይቅ የነበረው የትምህርት ቤቶች ደረጃ የማሳደግ ስራ ተገቢውን ምላሽ የሰጠ ፕሮጀክት ነው ብለዋል ።

የክልሉ መንግስት የትምህርት ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በተለይ ከትምህርት ጥራት ጋር ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በውጤት ላይ የተመሰረተ ግምገማ በማከናወን ለመፍትሔው የሚበጁ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን አስረድተዋል ።

የትምህርት ጥራት የሚለካው የዜጎች እውቀት፣ክህሎትና አመለካከት መለወጥ ሲቻል  ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይ መምህራን ወላጆችና የትምህርት ባለድርሻ አካላት በዚህ ላይ ሊረባረቡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የጀግኖች መታሰቢያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የፊዚክስ መምህር  ዳንኤል ማሞ እንዳሉት የማስፋፍያ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱ በትምህርት ቤቱ የመማርያ ክፍሎች የነበረውን መጨናነቅ ይቀርፋል ።

ግንባታው ተማሪዎች በቤተ ሙከራና ቤተ መጽሃፍት በመታገዝ የተሻለ እውቀት እንዲገበዩም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል ።

በሐረሪ ክልል በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ አስረኛ ክፍል ድረስ ከ75 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ይገኛሉ ተብሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም