ኢትዮጵያውያን ብስክሌተኞች የተሳተፉበት የቱር ሩዋንዳ ውድድር እንደቀጠለ ነው

91

አዲስ አበባ የካቲት 17/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን ብስክሌተኞች የተሳተፉበት የቱር ሩዋንዳ ውድድር የሶስተኛ ዙር ውድድሩን ዛሬ ያካሂዳል።

በውድድሩ ተመስገን መብራህቱ፣ ነጋሲ ኃይሉ፣ ክብረአብ ተክለሃይማኖት፣ ኃይለመለኮት ወልደአብዝጊና ፊልሞን ዘርዓብሩክ ኢትዮጵያን ወክለው በመሳተፍ ላይ ናቸው።

ሙሉ ክንፈ የፈረንሳዩን ኒፖ ዴልኮ ዋን ፕሮቬንቼን፣ ሀብተአብ ወልደገብርኤል የደቡብ አፍሪካውን ፕሮተች ክለቦችን ወክለው በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በሶስተኛው ቀን በሚካሄደው ውድድር 142 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን ትናንት በተደረገው የሁለተኛ ዙር የ120 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ውድድር የኒፖ ዴልኮ ዋን ፕሮቬንቼ ክለብ ተወዳዳሪው ሙሉ ክንፈ አሸንፏል።

ኃይለመለኮት 11ኛ፣ ፊልሞን 36ኛ፣ ክብረአብ 42ኛ፣ ተመስገን 57ኛ ደረጃዎችን በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በአንደኛና በሁለተኛ ዙር በተካሄዱት ውድድሮች ድምር ውጤት ሙሉ ክንፈ ዘጠነኛ፣ ክብረአብ ተክለሃይማኖት 26ኛ እና ፊልሞን ዘርዓብሩክ 38ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የካዛኪስታኑ ይቬግኒ ፌዶሮቭ በአጠቃላይ ድምር ውጤት የመሪነቱን ደረጃ የያዘ ሲሆን፣ ኤርትራውያኑ ሄኖክ ሙሉብርሃንና ቢንያም ኃይሉ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃዎችን ይዘዋል።

እስከ የካቲት 22 ቀን 2012 በሚቆየውና በስምንት ዙሮች የሚካሄደው ውድድር 889 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል።

በውድድሩ ላይ ሩዋንዳ፣ ካሜሩን፣ አልጄሪያና ኤርትራ ከአፍሪካ የሚሳተፉ ብሔራዊ ቡድኖች ሲሆኑ፣ ከአፍሪካ ውጭ ቤልጂዬም በመሳተፍ ላይ ነች።

ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2018 በተካሄደው ውድድር በቡድን ሶስተኛ በመውጣት ማጠናቀቋ ይታወሳል።