ታላቁ ሩጫ በዋግ ኸምራ በቅርቡ ትምህርት ቤት ሊገነባ ነው

48

አዲስ አበባ የካቲት 17/2012 (ኢዜአ) ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአማራ ክልል ዋግ ኸምራ በሁለት ሚሊዮን ብር ትምህርት ቤት ለመገንባት የገባውን ቃል በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታወቀ። 

ታላቁ ሩጫ በዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ትምህርት ቤት ለማስገንባት በገባው ቃል መሰረት በቅርብ ጊዜ የግንባታ ስራውን እንደሚጀምር አስታወቀ።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መስራችና ባለቤት ሻለቃ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ አስተዳደር ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ አንድ የዳስ ትምህርት ቤት በዘመናዊ መልኩ ማስገንባቱ ይታወሳል።

ከዚያ በኋላም ድርጅቱ በታላቁ ሩጫ በኩል ሁለተኛ ትምህርት ቤት ለማስገንባት ቃል ተገብቶ ነበር።

ቃሉን ጠብቆም በቅርቡ የትምህርት ቤቱን ግንባታ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን በተለይ ለኢዜአ አስታውቋል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አየለ እንደገለጹት ታላቁ ሩጫ በየዓመቱ በበጎ አድራጎት ስራው የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል።

በዚህ ዓመትም በበጎ አድራጎት ስራው የተያዘውን የ2 ሚሊዮን ብር በጀት ትምህርት ቤት ለመገንባት እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚሁ ገንዘብ በዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከሚገኙት የዳስ ትምህርት ቤቶች መካከል አንደኛውን በዘመናዊ መልኩ ለመገንባት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ ሲሆን በቅርቡም ግንባታው እንደሚጀመር አረጋግጠዋል።


ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ለበጎ አድራጎት የሚውል ገንዘብ በማሰባሰብ የተለያዩ እገዛዎችን እንደሚያደርግ ይታወቃል።

ባሉት አምስት ተከታታይ አመታት ብቻ በድምሩ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማበርከቱም ታውቋል።