ቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የአንበጣ መንጋን ለመከላከል 10 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የአንበጣ መንጋን ለመከላከል 10 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ

የካቲት 17/2012 (ኢዜአ) የቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በምስራቅ አፍሪካ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከልና በቀጠናው ያለውን የሰብአዊ ቀውስ ችግር ለመቅረፍ ለሚከናወኑ ተግባራት ነው 10 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደረገው፡፡
ድጋፉ ከተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ጋር አብረው ለሚሰሩ መንግሥታት የሚደረግ ሲሆን ኢትዮጵያ ፣ ኬንያና ሶማሊያ የድጋፉ ተጠቃሚ ናቸው፡፡
የጌትስ ፋውንዴሽን ድጋፍ ሀገራቱ የአንበጣ መንጋውን ለመዋጋት ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የእህል ምርቶችን ከአንበጣ ለመከላከል ለሚከናወነው ተግባር ከፍተኛ እግዛ እንደሚያደርግም ነው የተጠቆመው፡፡
"ፋኦ" የሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ላደረገው የድጋፍ ስራ ምስጋና ማቅረቡን ዘ ሳውዝ አፍሪካን አስነብቧል፡፡
በኢትዮጵያና ሶማሊያ ከ25 ፣በኬንያ ድግሞ ከ70 አመታት በኋላ በአስከፊ ሁኔታ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ወደ ጅቡቲና ኤርትራም መዛመቱ በመረጃው ሰፍሯል።
ደቡብ ሱዳን ኡጋንዳ ታንዛኒያ እንዲሁም በኢራን ደቡባዊ ምእራብ የባህር ዳርቻ የአንበጣ መንጋው ከታየባቸው ስፍራዎች መካከል ናቸው፡፡
ጥቂት በሚባል ደረጃ የሚከሰት የአንበጣ መንጋ በአንድ ጊዜ 35 ሺህ ሰዎች የሚመገቡትን እህል እንደሚያወድም "ፋኦ" ገልጿል፡፡
"ፋኦ" በቀጠናው ላይ ለሚታየው የምግብ እጥረት በዚህ አመት 76 ሚሊዮን ዶላር በጀትን ይዞ ቢቆይም ወደ 138 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ማድረጉን ዘ ሳውዝ አፍሪካን በድረ ገጹ አስነብቧል።