የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባው የባህልና ታሪክ ሙዚየም ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

65

ሶዶ፣ (ኢዜአ) የካቲት 17/2012 የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስገነባው የባህልና ታሪክ ሙዚየም ተመርቆ ለአገልግሎት ከፍት ሆነ።

በምረቃው  ስነሰርዓት ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ እንደገለጹት ሙዚየሙ የወላይታን ቅርስ፣ ታሪክና ባህላዊ ትውፊቶችን በአንድ ማዕከል አካቶ የያዘ  ነው።

ለጉብኝትና ለምርምር ግብዓትነት የሚያገለገል እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ከሚተገብራቸው የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶች የባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋና  የመስህብ ስፍራዎች እንዲሁም የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ስራ ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዝ ተናግረዋል።


ዩኒቨርሲቲው በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ላይ የጥናትና ምርምር ስራዎችንም ለማከናወን የዘርፉን ምሁራን በማሳተፍ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የታሪክ ባለሙያ ዶክተር ዘብዴዎስ ጫማ  በበኩላቸው "ሙዚየሙ ለባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ የመስህብ ስፍራዎች እና በቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዘርፍ የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለማጠናከር ብሎም ትውፊትን ለትውልድ በማስተላለፍ የማይተካ ሚና ይኖረዋል"ብለዋል፡፡


ሙዚየሙ  ከዩኒቨርሲቲው ምስረታ ጀምሮ እንዲገነባ  ህብረተሰቡ ሲቀርብ ለነበረው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት  በተያዘው ዓመት በአጭር ወራት ውስጥ ተሰርቶ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን አስረድተዋል።

ሙዚየሙ የተመረቀው  የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎችና ወጣቶች በተገኙበት ትናንት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም