የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በወረዳውና በክፍለ ከተማው ቸልተኝነት መብትና ጥቅማችን አልተከበረም አሉ

60

የካቲት አዲስ አበባ  ኢዜአ 17/2012  በወረዳውና ክፍለ ከተማው ቸልተኝነት መብቶቻችውና ጥቅሞቻቸው እንዳልተከበሩላቸው ለኢዜአ ቅሬታቸውን ያቀረቡ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ከፍለ ከተማ የወረዳ 13 ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ተናገሩ። 

የወረዳው ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ከ45 ሺህ በላይ ነዋሪዎች አገልግሎት ይሰጣሉ።

ባለሙያዎቹ አስቀድመው ከሰሩበት ወረዳ አንድ ጤና ጣቢያ ሕዝቡን በቅርበት ለማገልገል በወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት በተቋቋመው ጤና ጣቢያ ሲሰሩ ቆይተዋል።

ነገር ግን ባለፈው ዓመት መጨረሻ የተተገበረው የሰራተኛ ድልድል ባለሙያዎችን እንዳላካተተ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ክፍለ ከተማው ለወረዳው አንድ ጤና ጣቢያ 23 መደብ ፈቅዶ የጤና ባለሙያዎቹ እንዲመደቡበት ቢልክም፤ ጤና ጣቢያው ''ሠራተኛ ስለቀጠርኩ ቦታ የለኝም'' እንዳላቸወም ይገልጻሉ።

መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የፐብሊክ ሰርቪስ ጽህፈት ቤት የሰው ሃይል አመራር የአፈጻጸም ክትትልና ግምገማ ቡድን በላከው ደብዳቤ የጤና ባለሙያዎቹ በምደባው ባለመካተታቸው በአቅራቢያቸው ጤና ጣቢያ ምደባ እንዲሰጣቸው በድጋሚ አዟል።

ነገር ግን የዘርፉ ሃላፊዎች ጉዳዩን በቸልተኝነት በመመልከታቸው ሠራተኞቹ ጥቅሞቻቸውና መብቶቻቸው ሳይከበሩላቸው መቆየታቸውንም አስረድተዋል።

''ይህ ደግሞ በከፍለ ከተማው እንዲሁም በወረዳው ያለው የመረጃ መለዋወጥ ግልጽነት የጎደለውና የሰራተኛውን መብት ማስከበር ትኩረት እንዳልተሰጠው ማሳያ ነው'' ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሲስተር ሰብለ አእምሮና ሲስትር ሰብለወርቅ ጌታቸው ናቸው።

በተለይ የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ግልጽነትና የአሰራር ችግሮች እንዲፈጠሩ አድርጓል ያሉት ሲስተር ገነት አረጋ ናቸው።

መንግሥት የትምህርት እድልና ጥቅማ ጥቅሞች ቢፈቅድም፤ ሃላፊዎች ግልጽ የሆነ መረጃ ስለማይሰጡና ተከታትለው ስለማያስፈጽሙ ተጠቃሚ አላደረጉንም ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ከእነሱ እኩል ደረጃና የስራ ልምድ ያላቸው የጤና ባለሙያዎች ተጨማሪ የስድስት ወር ክፍያ እንደተከፈላቸው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል።

በሙያው ከአራት እስከ 10 ዓመት ያገለገሉ ቅሬታ አቅራቢዎች የሚመለከተው አካል  አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጤና ቢሮ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሲስተር ለይላ ከማል እንዳሉት፤ የሰራተኞቹ ጥያቄ ትክክል ቢሆንም ጉዳዩ ለማስፈጸም ጊዜ የፈጀው ቅንነት ባለመኖሩ ነው።

ጉዳዩ ለክፍለ ከተማው ከአቅምም በላይ መሆኑንና በወረዳው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እንደሚያስፈልጉ ቢታመንም ጉዳዩን የሚያስፈጽሙ የወረዳው ጽህፈት ቤት ቸልተኝነት ታይቶባቸዋል ብለዋል። 

በአቅራቢያው ባሉ ጤና ጣቢያዎች መደብ ተከፍቶላቸው እንዲመደቡ ቢጠየቅም አፋጣኝ ምላሽ አለመገኘቱንም ገልጸዋል።

ሰራተኞችም ጉዳያቸውን ለማስፈጽም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ስራ እየተበደለ መሆኑን ያስረዱት ሲስተር ለይላ፤ አዳዲስ ፕሮግራሞች ለማስጀመር መቸገራቸውንም ተናግረዋል።

የወረዳው ፐብሊክ ጽህፈት የሰው ሃብት ልማት ቤት ሃላፊ አቶ ገብረሕይወት ይብራህ በበኩላቸው ''ከተማው ቅሬታ አቅራቢዎችን ይመደቡ የሚል መመሪያ አላደረሰኝም። ስለዚህ ባልደረሰኝ መረጃ የደመወዝ ማስተካከያውም መስራት አልችልም'' ብለዋል።

መንግስት በላይኛው አመራር ያለውን ችግር ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት በወረዳና በክፍለ ከተማው ባለ የስራ ሃላፊዎች ላይ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ በስልክ በሰጠን ምላሽ ''ጉዳዩ በክፍለ ከተማና በወረዳ የሚያልቅ ነው'' ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም