በቡሬ ከተማ በ3 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነባው የዘይት ፋብሪካ እየተጠናቀቀ ነው

72

ባህርዳር፣ ኢዜአ፣የካቲት 16/2012(ኢዜአ) በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ከተማ 3 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ እየተገነባ ያለው የዘይት ፋብሪካ እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገለፀ ።


ፋብሪካው በተለያዩ የመንግስት ኃላፊዎች እየተጎበኘ ነው።
ፋብሪካው ፊቤላ በተባለ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተገነባ ሲሆን በቀን 1ነጥብ 4 ሚሊዮን ሊትር ዘይት የማምረት አቅም አለው

የፋብሪካው የኮንስተራክሽን ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ እንየው ዋሴ ለኢዜአ እንደገለጹት ፋብሪካው በ28 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው።

በአሁኑ ወቅት 95 ከመቶ ግንባታው የተጠናቀቀ ሲሆን የማሽን ተከላና ሌሎች የዝግጅት ሥራዎች በመጠናቀቃቸው በቀጣይ 3 ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ማምረት ስራ ይገባል ብለዋል።


ፋብሪካው ዘይት አምርቶ ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ የሠሊጥ ማቀነባበሪያ፣ የፕላስቲክ፣ የካርቶን፣ የሣሙናና ማርጋሪን ማምረቻ ፋብሪካዎች እንደሚኖሩት ጠቁመዋል።


የፋብሪካው የግንባታ ሒደት ከንግድ ሚኒስቴርና ከአማራ ክልል ንግድ ቢሮ በተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች እየተጎበኘ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም