የባሌ ዞን ሮቤ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች የድጋፍ ስልፍ አካሄዱ

58

የካቲት 16/2012(ኢዜአ) በሀገሪቱን የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ከዳር እንዲደርስ ከመንግስት ጎን ተሰልፈው የድርሻቸውን እንደሚወጡ በባሌ ዞን የሮቤ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ባካሄዱት የድጋፍ ሰልፍ ገለጹ።

ነዋሪዎቹ  ዛሬ በሮቤ ከተማ  ባካሄዱት ሰልፍ ድጋፋቸውን የገለጹት የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማትና በሰጡት አስተያየት ነው።

"ጅምራችን መደመር መዳረሻችን ብልፅግና፣ በመንደርተኝነት አስተሳሰብ የኦሮሞ ህዝብ ለመከፋፈል የሚጥሩትን እንቃወማለን፣ መጪው ጊዜያችን ከዶክተር አብይ ጋር ብሩህ ነው፣ ከመንግስት ጎን ቆመን ሀገሪቱን እናሻግራለን” የሚሉ ካሰሟቸው መፈክሮች  ይገኙበታል።

ከሰልፈኞቹ መካከል አቶ ሙስጠፋ ሀሰን በሰጡት አስተያየት በዶክተር አብይ አህመድ መሪነት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ችግሮችን ለመፍታት እያደረጉ ያሉትን ጥረት ለመደገፍና እውቅና ለመስጠት ሰልፍ መውጣታቸውን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሰላም፣ ፍቅርና አንድነት የሰጡት ዋጋና የመጣው ለውጥ ለድጋፍ እንዲወጡ ያነሳሳቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

"ለእውነትና አንድነትን የቆሙ የኢትዮጵያ መሪ መሆናቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በተግባር ባከናወኗቸው ሥራዎችና ባመጧቸው ለውጦች አረጋግጠናል" ያለው ደግሞ ወጣት መስፍን ከተማ ነው፡፡ 

ወይዘሮ ከድራ ሁሴን በበኩላቸው "የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ከዳር እንዲደርስ በአንድነት መንፈስ መንቀሳቀስ አለባቸው" ብሏል፡፡ 

በድጋፍ ሰልፉ ሲሳተፉ  ከምስጋና ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመደገፍ ለውጡ እንዲሳካ  ከጎናቸው መቆማቸውን ለማሳየት በራሳቸው ተነሳሽነት ሰልፍ  እንደወጡ ሌላው ተሳታፊ አቶ  አህመድ ከድር ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የተጀመሩ ለውጦች ከዳር እንዲደርሱ ከዶክተር አብይ ጎን በመሰለፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል፡፡

ወይዘሮ ሀሊማ ኡስማን በበኩላቸው  ሀገራዊ ለውጡ ከዳር እንዲደርስ ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ ተናግረዋል፡፡

የሮቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱልጀሊል አብዱሮ ለሰልፈኞቹ ባደረጉት ንግግር የመደመር አስተሳሰብ የኢትዮጵያን ህዝቦች አንድነት ለማዳበር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

ዶክተ አብይ ለመላው የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ትስስርና መደጋገፍ ጭምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰው  ህዝቡ ለውጡን ከዳር እንዲደርስ  ድጋፉን ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

የምዕራብ ባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሀጂ  እንዳሉት የተጀመሩ ሀገራዊና ክልላዊ ለውጦች ለማሳካት የዞኑ ነዋሪዎች በአንድነት ሊቆሙ ይገባል።

ለልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠትም እንዲቻል  ከመንግስት ጎን በመቆም ድጋቻወን አንደቀጥሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም