የመላው ምስራቅ ሐረርጌና ወለጋ ዞኖች የስፖርት ውድድር ተጀመረ

123

ሀረር/ ነቀምቴ ኢዜአ የካቲት 16/2012፡- የመላው ምስራቅ ሐረርጌ እና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች የልዩ ልዩ ስፖርቶች ውድድር ተጀመረ።

በባቢሌ ከተማ ዛሬ የተጀመረው የመላው ምስራቅ ሐረርጌ ዞን  የስፖርት ውድድር እስከ የካቲት 25 ቀን 2012 ዓ .ም. የሚቆይ ሲሆን ከ20 ወረዳዎችና አራት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ1ሺ 600 በላይ ስፖርተኞች በሁለቱም ጾታ ይሳተፋሉ።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አባድር አሚኖ በመክፈቻ ስነሰርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት ዛሬ የተጀመረው ውድድር ወጣቶች እርስ በርስ ተቀራርበው ተሞክሮ እንዲለዋወጡና እድል ያላገኙ ስፖርተኞች አጋጣሚውን እንዲጠቀሙ ያስችላል።

ስፖርተኞቹም  ጨዋነት በተላበሰ ሁኔታ ውድድራቸውን እንዲያካሂዱ አሳስበው የዞኑ የስፖርት እንቅስቃሴ ለማጎልበት አስተዳደሩ  ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ዓላማውም ከመጋቢት 6 እስከ መጋቢት 20/2012ዓ.ም. በሰበታ ከተማ በሚካሄደው የመላው ኦሮሚያ ስፖርት ጨዋታዎች  ዞኑን ወክለው የሚወዳደሩ ስፖርተኞችን ለመመልመል የተዘጋጀ ነው።

እግር ኳስ፣ቦሊቦልና  ጠረጴዛ ቴንስን ጨምሮ በስምንት የስፖርት ዓይነቶች በውድድሩ እንደሚካሄዱ የዞኑ ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፋዮ ሰዒድ ገልጸዋል።

በመክፈቻው ስነሰርዓት የዞኑ እና የየወረዳ አመራሮች  የተገኙ ሲሆን በዕለቱ  በባቢሌ እና ቀርሳ ወረዳ መካከል በተካሄደው እግር ኳስ ውድድር ባዶ ለቦዶ ተለያይተዋል።

በተመሳሳይ የመላው ምስራቅ ወለጋ ዞን  የወረዳዎች የስፖርት ሻምፒዮና ውድድር በነቀምቴ የወለጋ ስታዲዮም እየተካሄደ ነው።

ውድድሩ ትላንት   ሲጀመር የዞኑ የስፖርት ጽሀፈት ቤት  ኃላፊ አቶ ዮሃንስ ቢየና እንዳሉት ጨዋታው እስከ 27 /2012 ዓ.ም. የሚቆይ ሲሆን 17 ወረዳዎችና አንድ የከተማ አስተዳደር የተወጣጡ በሁለቱም ፆታ  ከ1ሺህ በላይ ስፖርተኞች ለመሳተፍ ተዘጋጅተዋል።

ከጨዋታዎቹ መካከል እግር ኳስ፣ ቦሊቦል፣ አትሌቲክስና  በፓራኦሎምፒክ ይገኙበታል።

የውድድሩ ዓላማ  በወረዳዎቹ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከርና  የመላው የኦሮሚያ ስፖርት ጨዋታዎች ላይ ዞኑ የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመመረጥ ነው።

በመክፈቻው ዕለት በእግር ኳስ  ሲቡ ስሬ ወረዳ የጅማ አርጆ አቻውን አስተናግዶ ሶስት ለአንድ በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በወንዶች 5ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ከፍያለው ተረፈ ከሊሙ ወረዳ፣ ሀብታሙ ፍቃዱ ከሌቃ ዱለቻ ወረዳ፣ ሶሬሳ ጌታቸው ከሊሙ ወረዳ በቅደም ተከተል አንደኛ እስከ ሶስተኛ  ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል፡፡

በ1ሺህ 500 ሜትር የሴቶች የሩጫ  ደግሞ  ለሊሴ ገመቹ ከዋዮ ቱቃ ወረዳ፣ ጃለኔ ብርሃኑ ከቦነያ ቦሼ ወረዳ እና እየሩሳሌም ቶላ ከዋዮ ቱቃ ወረዳ እንዲሁ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ወጥተዋል።

   
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም