በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሊጉን መሪነት ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ተረከበ

73

የካቲት 16/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማን በማሸነፍ የሊጉን መሪነት ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ተረከበ።

የሊጉ 8ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜና እሁድ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ተካሂደዋል።

በሳምንቱ ይጠበቅ የነበረው የቂርቆስ ክፍለ ከተማና የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ጨዋታ ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ተካሂዶ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ 32 ለ 25 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ በውድድር ዓመቱ አንድ ጊዜ ብቻ የተረታው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነጥቡን ወደ 14 ከፍ በማድረግ የሊጉን መሪነት ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ተረክቧል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ይካሄዳል ተብሎ የጨዋታ መርሃ ግብር ወጥቶለት የነበረው የፌዴራል ማረሚያ ቤቶችና የሊጉ አዲስ ተሳታፊ ሚዛን አማን ከተማ ጨዋታ ሚዛን አማን ባለመገኘቱ በውድድሩ መመሪያ መሰረት ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የሁለት ነጥብና የ10 ለ 0 የፎርፌ ውጤት አግኝቷል።

ከትናንት በስቲያ በክልል ከተሞች በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ቡታጅራ ከተማ በሜዳው በምባታ ዱራሜ 20 ለ 19 በሆነ ውጤት ሲሸነፍ፤ ወደ ጎንደር ያቀናው ፌዴራል ፖሊስ ጎንደር ከተማን 20 ለ 18 ማሸነፍ ችሏል።

መቐለ ሰብዓ እንደርታና መከላከያ በፕሪሚየር ሊጉ ስምንተኛ ሳመንት መርሃ ግብር ጨዋታ ያላደረጉ አራፊ ክለቦች ናቸው።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ14 ነጥብ ሲመራ መቐለ ሰብዓ እንደርታና ከምባታ ዱራሜ በተመሳሳይ 12 ነጥብ በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

መቐለ ሰብዓ እንደርታና ከምባታ ዱራሜ በተመሳሳይ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ አላቸው።

ሚዛን አማን ከተማ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 10ኛ ደረጃ ይዟል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትናንት በክልል ከተሞች ተካሄደዋል።

በሴቶች ጅማ ላይ ወልቂጤ ከተማ አዲሱን የሊጉን ተሳታፊ ጅማ ከተማን 74 ለ 47 እንዲሁም ጎንደር ላይ ሀዋሳ ከተማ ጎንደር ከተማን 46 ለ 18 በሆነ ሰፊ ልዩነት አሸንፈዋል።

በወንዶች ወልቂጤ ከተማ አዲሱን የሊጉ ተሳታፊ አጋዚ ውቅሮን አስተናግዶ 87 ለ 15 በሆነ ሰፊ ልዩነት ሲያሸንፍ ጎንደር ላይ የአምናው አሸናፊ ሀዋሳ ከተማ ጎንደር ከተማን 66 ለ 39 ረትቷል።

በሴቶች አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን በወንዶች የካ ክፍለ ከተማ በሶስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ጨዋታ ያላደረጉ ክለቦች ናቸው።