የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ኢትዮጵያን እንድናውቅና ኢትዮጵያዊነትን እንድናዳብር ያግዛል - ተሳታፊ ወጣቶች

153
አዲስ አበባ የካቲት 15/2012 (ኢዜአ) የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ኢትዮጵያን እንድናውቅና ኢትዮጵያዊነትን እንድናዳብር ያግዛል ሲሉ ዛሬ በተበሰረው የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች ተናገሩ። ከሁለት ወር ስልጠና በኋላ ወደ በጎ አድራጎት ተግባራት የሚሰማሩት ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢ የተውጣጡ በመጀመሪያው ዙር ከ10 ሺህ በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃን ናቸው። መርሃ ግብሩ ዛሬ በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ ሲበሰር ኢዜአ መድረኩን የታደሙ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን አነጋግሯል። ብዙዎቹ ወጣቶች ከዚህ በፊትም በተለያየ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ልምድ እንዳላቸው በመግለጽ፤ ተሞክሯቸውን ይበልጥ በማስፋት የህሊና እርካታ ለማግኘት እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል። ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁት ወጣት አበበ አዲሱ፣ ረድኤት አለማየሁና ጀማል መሀመድ በመርሐ ግብሩ ተሳታፊ መሆናቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ በሚመደቡበት ሁሉ ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። በሌላ በኩል በበጎ አድራጎት ተሳታፊዎች ከትውልድ ቀዬአቸው ተለይተው በሌሎች አካባቢዎች ስለሚሰማሩ ኢትዮጵያን ለማወቅ፣ ኢትዮጵያዊነትንም ለማጠናከር ያግዛል የሚል እምነት አላቸው። ለስራ ፈጠራና የሕይወት ተሞክሮን ከማስፋት በተጨማሪ የሌሎች አካባቢ ማህበረሰቦችን ወግና ልማድ ለማወቅ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል። ከአርሲ ዞን የመጣው ጃርሶ ሃይሉ፣ ከድሬዳዋ የመጡት ሰናይት ደረጀና ፈቲያ ሸምሱ እንዲሁም የአዲስ አበባው ወጣት አንማው መንጌ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብሩ ፋይዳ ላይ ይስማማሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ተወካይ በኮሚሽኑ የሰው ሀብት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽነር ሳራ አንያንግ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድርና ሚኒስትሮች በተገኙበት መርሃ ግብሩ ዛሬ በይፋ ተበስሯል። በአገር አቀፍ ደረጃ የሚተገበረው በዚህ መርሐ ግብር ከ100 ሺህ በላይ ወጣቶች የተመዘገቡ ሲሆን በመጀመሪያ ዙር የተመለመሉት 10ሺህ ወጣቶች ለአንድ ዓመት ከሁለት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያበረክታሉ። በዚህ በጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት የሚሳተፉት ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃን ስራ ፈላጊ ወጣቶች ሲሆኑ ቀጥታ ስራ ከመጀመራቸው በፊት ለሁለት ወራት የስብዕና፣ አካላዊና ስራ ፈጣሪነት ስልጠናዎች እንደሚወስዱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም