ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት የሃይል እጥረት ማነቆ ሆኖብኛል--የአዲስ አበባ ስራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ

83
አዲስ አበባ የካቲት 15/2012 ( ኢዜአ)  የተደራጁ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት የሃይል እጥረት ማነቆ እንደሆነበት የከተማዋ የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡ የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ ''የትራንስፎርመር እጥረት ስላለብኝ ችግሩን መፍታት አልቻልኩም'' ብሏል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ተድላ አጥናፉ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ የከተማ አስተዳደሩ ለዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር በትጋት እየሰራ ነው። ባሣለፍነው በጀት ዓመት መጨረሻ የ469 ሼዶችና የሰባት ህንጻዎችን ግንባታ በማጠናቀቅ ለኢንተርፕራይዞች ለማስተላለፍ ዝግጁ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ግንባታቸው ተጠናቀው ለወጣቶች ለመተላለፍ ዝግጁ የሆኑ ሼዶችና ህንጻዎች በሃይል እጥረት ከስምንት ወር በላይ ተዘግተው መቀመጣቸውን ተናግረዋል፡፡ ለአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከሁለት ዓመት በፊት ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ መክፈላቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ በተፈጠረው የሃይል እጥረት ምክንያት 3 ሺህ 700 የሚሆኑ ስራ ፈላጊዎችን ወደ ስራ ማስገባት እንዳልተቻለ አቶ ተድላ አስረድተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተጠየቀውን 81 ትራንስፎርመር በአፋጣኝ እንዲያቀርብም አሳስበዋል፡፡ ችግሩ በአፋጣኝ ከተፈታ ተደራጅተው ሃይል በመጠባበቅ ላይ ያሉ ስራ ፈላጊዎች በፍጥነት ወደ ስራ ይገባሉ ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ የትራንስፎርመር አቅራቢ ድርጅቶች በውላቸው መሠረት ማቅረብ ባለመቻላቸው ችግሩ እንዳጋጠመው ገልጸዋል። የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ክፍሌ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የትራንስፎርመር አቅራቢዎች የአቅም ውስንነት እንዳለባቸው ገልጸዋል። የአዲስ አበባ የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ያቀረበው ቅሬታ ተገቢ መሆኑንም አምነዋል። ከተቋሙ ጋር ውል የፈጸሙ የትራንስፎርመር አምራች ድርጅቶች ውላቸውን  አክብረው ትራንስፎርመሩን ማቅረብ ከቻሉ ችግሩን መፍታት እንደሚቻል አመልክተዋል። ችግሩ በዚህ በጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ እንደሚፈታም ጨምረው ተናግረዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም