በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 14 ክላሽ ጠብመንጃ ተያዘ

117
መቱ የካቲት 15/2012 (ኢዜአ) በኢሉ አባቦር ዞን ቡሬ ወረዳ በህገወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 14 ክላሽኮቭ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ ገለፀ :: የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ታረቀኝ አሰፋ እንደገለፁት የጦር መሳሪያው የተያዘው  በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 አማ 21199 በሆነ ሚኒባስ ተሽከርካሪ ከጋምቤላ ወደ አዲስ አበባ በመጓጓዝ ላይ እንዳለ ነው ። መሳሪያዎቹ ዛሬ ጠዋት 2 ሰዓት ተኩል አካባቢ በቡሬ ከተማ በተደረገው ፍተሻ በተሽከርካሪው ውስጠኛው አካል በላሜራ በተበየደ ቦታ ውስጥ ተደብቀው ተገኝተዋል ። የሚኒባሱ አሽከርካሪ ለጊዜው መሰወሩን ገልፀው ሌሎች በውስጥ የነበሩ ሁለት ሰዎች ግን በቁጥጥር ስር ውለዋል ። አሽከርካሪውን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ኮማንደሩ ገልፀው በቁጥጥር ስር በዋሉት ግለሰቦች ላይ ማጣራት እንደሚካሄድ ተናግረዋል:: አካባቢው በተደጋጋሚ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ሲደረግ የሚያዝበት በመሆኑ ጥብቅ ቁጥጥር እየተካሄደ መሆኑንም ኮማንደር ታረቀኝ ገልፀዋል ። ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ እንቅስቃሴውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኮማንደሩ ጠይቀዋል::  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም