‘’ ጥረት--የስኬት ግብአት’’

161
ከአማረ ኢታይ መቀሌ ኢዜአ ወጣቶች ሁሌም ከስኬትም ከውድቀትም ጋር አብሮው የሚኖሩ ናቸው ። ሁሉንም ነገር ይቻላል ። የማይቻል ነገር የለም የሚሉ፣በጥረት የሚያምኑና በተስፋ የተሞሉ ወጣቶች ደግሞ ስኬትን ይጎናጸፋሉ። የተቃራኒ ጉዞ የሚመርጡና ፊታቸውን እንደ ሐምሌ ሰማይ ያጨፈገጉ እንዲሁም እጅና እግራቸውን አጣጥፈው የሚቀመጡ ወጣቶች ደግሞ ውድቀትን ተከናንበው  መጥፎ ህይወትን ለመግፋት ይገደዳሉ ። በኢትዮጰያ ዜና አገልግሎት የትግራይ ማስተባባሪያ ሪፖርተሮች የትግራይ ክልል ወጣቶችን የስራ ጥረትና ትጋት አስመልክተው ሰሞኑን የዘገቡዋቸው የስኬት ዘገባዎች ይህንን የሚመሰክሩ ናቸው ።ዘገባዎቹ ቀልብን የሚስቡና ለጆሮ ምቾት የሚሰጡ ነበሩ ። ወጣቶች ሌት ተቀን ከጣሩ ህልምና ቅዠት የሚመስለው ነገር ሁሉ እንደሚደርሱበት ማሳያ ናቸው ። ወደ ስራው ሲገቡ ትንሽ የመነሻ ገንዘብ ይዘውና ብዙ ተስፋ ሰንቀው እንደነበር በአንደበታቸው ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። በመቀሌ ከተማ በአልባሳት የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ሦስት ወጣቶች ወደ ባለሃብትነት መሸጋገራቸውን ይናገራሉ ። በዘርፉ ከተሰማሩ እና የስኬት ጉዞን መቆናጠጥ ከጀመሩ ወጣቶች መካከል ወጣት ያሬድ አስገዶም አንዱ ነው። ከሰባት ዓመታት በፊት በመቀሌ ከተማ  ኩሓ ክፍለ ከተማ በሚገኝ "ማ- ጋርመንት" በተባለ የግል የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ተቀጥሮ ስራ መጀመሩን ያስታውሳል። ወጣት ያሬድ ከጅምሩም ህልምና መልካም ራእይ የሰነቀ ነውና ለሁለት ዓመታትያህል ተቀጥሮ በሰራበት ፋብሪካ ሁለት ነገሮች ማግኘቱን ይገልጻል ። ጥረቱና ፍላጎቱን እውን የሚያደርጉለት የስራ ባህልና ክህሎት ናቸው ። እነዚህም የራሱን የአልባሳት ስራ እንዲጀምር ወኔም መነሳሳትም ፈጥረውልኛል ይላል። "በፋብሪካው የሁለት ዓመት ቆይታዬ የስራ ክቡርነት መረዳቴን ብቻ ሳይሆን በትንሽ ነገር ስራ መጀመር እንደሚቻል የተማርኩበት የተግባር ዩኒቨርስቲዬ ነው " ይላል። ወጣት ያሬድ በኋላም በፍላጎትና በስራ ታታሪነቱ ከሚመሳሰለው ሌላ ጓደኛው ጋር በመሆን በ450 ሺህ ብር የመነሻ ካፒታልና ሶስት የስፌት ማሽኖችን በመያዝ ቤት ተከራይተው ስራቸውን አሃዱ ብለው ጀመሩ። የጀመሩት ስራ ቀስ በቀስ ውጤታማ እየሆነ መሄዱን የሚናገረው ወጣት ያሬድ ዛሬ ላይ የ13 ሚሊዮን ብር ካፒታል ባለቤቶች መሆን ችለዋል ። ስራቸውም እያደገና እየተመነደገ በመሄዱ ከተቀጣሪነት ወደ ቀጣሪነት ተሻጋግሯል ። ለ135 ዜጎችም ተጨማሪ የስራ እድልና የለመለመ ተስፋ ይዘውላቸው ብቅ ማለታቸውን ይናገራል። የባለብዙ ራእይና ተስፋ ባለቤት የሆኑ ወጣት ያሬድና ጓደኛው በተሻለ ካፒታልና የሰው ሃይል ዘርፉን አጠናክረው ለመቀጠል ከውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ይገልጻል ። ለክልሉ መንግስትም ተጨማሪ የቦታ ጥያቄ በማቅረብ በቂ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ይናገራሉ። በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ ባገኘው የቴክኖሎጂ እውቀትና የስራ ፍቅር በዘርፉ ለመሰማራት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረለት የተናገረው ደግሞ ሌላው የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ወጣት ጥዑማይ ካሕሱ ነው ። አሁንም በመቀሌ በዘርፉ ከተሰማራው "ዲ.ቢ.ኤል." ተብሎ ከሚጠራው የውጭ ኩባንያ የሙያ ስልጠና በቅርበት እያገኘ መሆኑን ይገልጻል። ወጣት ጥዑማይ እንደሚለው ከሶስት ዓመታት በፊት በሶስት የልብስ ስፌት ማሽኖችና በ150 ሺህ ብር ካፒታል የ"ጋርመንት" ስራ መጀመሩን ይናገራል።ዛሬ ላይ በሦስት ማሽኖች የጀመረው ስራ በ10 እጥፍ አድጎ የ30 ልብስ ስፌት ማሽኖችን ባለቤት ሆኗል ። ‘’ጥረት የስኬት ምንጭ ነው’’ የሚለው ወጣት ጥዑማይ፣በከፈተው የልብስ ስፌት የስራ ዘርፍ ለ32 ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል ። ካፒታሉንም ወደ 1 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ማድረስ ችሏል። በቀጣዮቹ አራት ዓመታትም የያዘውን ስራ ወደ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የማሳደግ እቅድ እንዳለው ነው የሚገልጸው። በመቀሌና አካባቢው ያሉት የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ወጣቶች የስራ መደላድል እየፈጠሩ መሆናቸውን የሚገልጸው ደግሞ ወጣት ጸጋይ ሐድጉ ነው። "እነሱ ባይኖሩ ኖሮ በየሰፈሩ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የተሰማሩ የጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ተቋማት አይበራከቱም ነበር" ባይ ነው ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተስፋፉ የመጡ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ለወጣቶች የስራ መንሳሳትና የእውቀት ምንጭ ሆነው እያገለገሉ መሆናቸውንም ይናገራል ። ወጣት ጸጋይ በፋብሪካዎቹ እውቀትና የስራ ባህሉን አሳድጎ በጋርመንት ዘርፍ እንዲሰማራ መንገዱን እንደከፈቱለት ነው የሚገልጸው። በሶስት ዓመታት የስራ ቆይታውም ለ15 ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠሩም በተጨማሪ የካፒታሉ መጠን ከ150 ሺህ ብር ወደ 750 ሺህ ብር ከፍ ማለቱን ይናገራል ። የ"ጋርመንት" ስራውን ለማስጀመር በፋብሪካዎቹ የሰለጠነና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል መገኘቱ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ማገዙን ያስረዳል ። በተጨማሪም የወጣቱን ጥረት እንዲጨምር፣ዓላማ እንዲኖረውና መልካም ራእይ ይዞ ወደ ፊት እንዲጓዝ ጠቃሚ ግብአት እንደፈጠሩለት አይካድም ባይ ነው ። የመቀሌ ከተማ አስተዳደር አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ገብረስላሴም የወጣቶችን አስተያየት ይጋሩታል ። በአሁኑ ወቅት በመቀሌ ከተማ አራት ሺህ የሚጠጉ ኢንተርፕራይዞች ከስድስት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ፈጥረዋል ። የክልሉ መንግስት በጨርቃ ጨርቅ  ዘርፍ ለተሰማሩት ወጣቶች የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ከማዘጋጀት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎች እያደረገ መሆኑንም ኃላፊው ይገልጻሉ ። ድጋፉም  በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት የማምረት ስራ የተሰማሩ ወጣቶች ወደ ባለሀብትነት የመሸጋገር ሚስጥርም ይኸው ነው ይላሉ። ‘’ሃብት ከፈለግክ መሬትን በደንብ ቅረባት፣ሚስጥሯዋን በሚገባ ተረዳላት፣አትርገጣት በደንብ ቆፍራት ። ከተቻለህ እንደ ገበሬ አፍቅራት ‘’የሚለውን የአንድ የቢዝነስ ከፍተኛ ምሁር አባባል በተግባር ያስመሰከሩ ወጣቶች ደግሞ ከትግራይ ክልል ከወደ ምስራቃዊ ዞን ብቅ ማለታቸውን ይበልጥ የምሁሩ አባባል እውነታውን ያጎላዋል። በዞኑ በእንስሳት ሀብት ልማት የተሰማሩ ወጣቶችተመሳሳይ ጥረትና ሃብትን የማፍራት ጽኑ ፍላጎት ይዘው ወደ ስራ በመሰማራታቸው የስኬት ጉዞን መጀመራቸውን ይናገራሉ ። ከተቀጣሪነት ወደ ባለሃብትነት መሸጋገርም ጀምረዋል። በዞኑ በክልተ አውላዕሎ ወረዳ የአይናለም ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ጌታቸው ወልደአብርሃ ከእነዚህ ታታሪ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው ። ከአራት ዓመት በፊት በሰው ሃብት ልማት አስተዳደር በመጀመሪያ ዲግሪ ከተመረቀ በኃላ በአንድ የግል ኩባንያ በ2 ሺህ 500 ብር ወርሃዊ ደመወዝ ተቀጥሮ ይሰራ እንደነበር ያስታውሳል ። ”ከወርሃዊ ደመወዝ ጠባቂነት የራሴን ስራ መፍጠር አለብኝ” የሚል ጽኑ ፍላጎትና ጠንካራ የስራ መነሳሳትን በመያዝ ወደ ዶሮ እርባታ መግባቱን ይናገራል ። ወጣት ጌታቸው በ500 ሺህ ብር የመነሻ ካፒታል በ2010 ዓ.ም ስራው መጀመሩን ይገልፃል። ዛሬ የሆነው እውነታ ማመን በሚከብድ መልኩ ወጣት ጌታቸው እጅግ ተለውጧል ። ከ2 ሺህ በላይ እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን አሉት ። በየወሩ ከ36 ሺህ በላይ እንቁላሎች በማምረት ላይ ነው ። በአከባቢው ለሚገኙ ሆቴሎች፣በጥቃቅንና አንስተኛ ንግድ ዘርፍ ለተሰማሩ ወጣቶች በማስረከብ ውጤታማ መሆኑን ይገልጻል። ከእንቁላል ሽያጭ ብቻ በወር ከ126 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኝ ነው ወጣት ጌታቸው ተወደአብርሃ የሚገልጸው። ሌሎች ወጣቶችም አርአያነቱ እንዲከተሉ መልካም ተሞክሮውንና ልምዱን እያካፈለ እንደሚገኝ ይገልጻል። ወጣቱ ዛሬ የስኬት ማማን ተጎናጽፎ 2 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር የሚገመት ካፒታል በማንቀሳቀስ ላይ ሲሆን ለ10 ወጣቶችም በዘርፉ የስራ እድል ፈጥሯል ። የወጣቱ አብሮ አደግና ጓደኛ ወጣት አብረሃለይ ሃሪፈዮ ስለ ጌታቸው ምስክርነቱን ሲሰጥ እንዳለው ጌታቸው  የቅርብ ጓደኞው ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ወጣቶችም መልካም ምሳሌ ነው ይለዋል። ለገንዘብ ፍላጋ ሲሉ በህገወጥ ስደት ምክንያት በየመንገዱ ህይወታቸውን ለሚያጡ ወጣቶችም በሀገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ወጣት ጌታቸው ወልደአብርሃ ጥሩ ማሳያ ነው ብሏል። በዓዲግራት ከተማ በማህበር ተደራጅተው ውጤታማ ከሆኑ ወጣቶች መካከል በከብት ማድለብና ወተት ሃብት ልማት ዘርፍ የተሰማሩየእነ ወጣት ሚከኤለ አስገዶም ማህበርም ተጠቃሽ ነው። የማህበሩ አባላት ከአንድ ዓመት በፊት ከቤተሰቦቻቸውና ከደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ባገኙት 950 ሺህ ብር ብድር 40  የውጭ ዝርያ ያላቸው የወተት ላሞችና በሬዎችን ገዝተው በማድለብና በመንከባከብ የወተት ምርትን የማከፋፈል ስራ በማካናወን ላይ እንደሚገኙ ወጣት ሚከኤለ ይገልፃል። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥም 75 የደለቡ ሰንጋዎችን ወደ  ገበያ ማቅረብ የሚችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ያብራራል።ማህበሩ በአሁኑ ወቅት ካሉት 30 የወተት ላሞች በቀን በአማካይ 400 ሊትር ወተት ለገበያ በማቅረብ በአንድ ዓመት ውስጥ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ካፒታል ማስመዝገባቸውን አመልክቷል ። ከወጣቶቹ ብዙ መማር ይቻላል ። ከሁሉም በላይ ግን ጥረትን፣ጽኑ ፍላጎትንና የስራ ታታሪነትን ምን ያህል ስኬትን ለመጎናጸፍ ጠቃሚ ግብአቶች መሆናቸውን በእርግጠኝነት መማር ይቻላል ። ሌሎች ወጣቶችም ከስኬታማ ወጣቶቹ መልካም ተሞክሮ በመውሰድና ያለፉበትን ጉዞ በመከተል ከድህነት አረንቋ መውጣት የሚችሉበትን መንገድ መከተል ይገባቸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም