የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራን በጥናትና ምርምር መታገዝ እንዳለበት የውጭ ተመራማሪዎች ተናገሩ

174
የካቲት 14/2012 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል በህዝብ ነጻ ጉልበት እየተካሄደ ያለውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በጥናትና ምርምር መታገዝ እንዳለበት የጃፓንና ጀርመን ተመራማሪዎች ተናገሩ። ተመራማሪዎቹ በክልሉ ምስራቃዊ ዞን በክልተ አውላዕሎ ወረዳ ፃዕዳናዕለ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ተገኝተው  የህዝቡን የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ እንቅስቀሴን በመስክ ተመልክተዋል። በጃፓን አለምአቀፍ ግብርና ሳይንስ ጥናት ማዕከል የአካባቢ ደን ከፍተኛ ተመራማሪ ሚስተር ታኬናካ ኮይቺ እንደተናገሩት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ትኩረት ተደርጎ መስራቱ  አዋጭነቱ የጎላ ነው። "ነዋሪዎቹ  በአካባቢ ጥበቃ ላይ እያደረጉት ያለውን ስራ አፈርን በጎርፍ ከመከላት የሚከላከል ከመሆኑ በተጨማሪ የሰብል ምርት እንዲጨምር ያደርገዋል "ብለዋል። ስራው ከአርሶ አደሩ በተጨማሪ ምሁራንም  ከአርሶ አደሮችን ጋር በመሆኑን  መስራት ይጠበቅባቸዋል"  ሲሉም ተናግረዋል። አርሶአደሮቹ በነጻ ጉልበት እያካሄዱት ያለውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ አካባቢያቸው ለማልማት እያደረጉት ያለውን ጥረት ሊመሰገኑ እንደሚገባ  አመልክተዋል። "በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ማህበረሰብ ተኮር የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ስኬታማ እንደሆነ በተግባር አይቻለሁ" ያሉት ደግሞ በጀርመን ሃምቡርግ ዩኒቨርሲቲ የመልክአ ምድርና የተፈጥሮ ጥበቃ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ኡዶ ስቺኪሆፍ ናቸው። በሌሎች ሀገራት  ህዝብን መሰረት ያላደረገ በመሆኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ስኬታማ ሳይሆን መቅረቱን ገልጸዋል። "በኢትዮጵያ  ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን ህዝብን መሰረት ያደረገ  የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ  በስኬታማናነቱ ለሌላው አለም ምሳሌ የሚሆን ነው "ብለዋል። ዝናብ አጠር በሆኑ  አከባቢዎች እርጥበትን ለመቋጠርና የአከባቢው ስነምህዳር ለመጠበቅ ህዝብን ያሳተፉ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ አዋጪ መሆኑን እንደተረዱም  ገልጸዋል። የህዝቡን ታታሪነትና ጥንካሬ ተመራማሪዎቹ አድንቀዋል። "በክልሉ እየተከናወነ ያለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በጥናትና ምርምር የታገዘ እንዲሆን  የመቀሌ  ዩኒቨርሲቲ  ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እየሰራ ይገኛል" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የአፈር ለምነት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ምትኩ ኃይሌ ናቸው። ፕሮፌሰር ምትኩ እንዳሉት በትግራይ በተካሄዱ የአፈርና ውሀ ጥበቃ  ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ ሆናለች። በክልሉ  የካቲት 3/2012ዓ.ም.  ተጀመረውና ለ20 ቀናት በሚቆየው  የዘመኑ  የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ አንድ ሚሊዮን 200ሺህ   እየተሳተፈበት መሆኑን ቀደም ብለን ዘግበናል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም