የቅደመ አክሱም ቅሪተ አካል ለጥናትና ምርምር እያገለገለ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ገለጹ

102
አክሱም፣ የካቲት 14/2012(ኢዜአ) የቅድመ አክሱም ስልጣኔ ቦታ የነበሩ ጥንታዊ ስፍራዎች እና ቅረተ አካል በዓለም አቀፍ የ የአርኪዮሎጂ ጥናትና ምርምር ማዕከልነት እያገለገሉ መሆናቸውን የዘርፉ ምሁራን ገለጹ። የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ከጀርመን አርኪዮሎጂ ኢንስቲዩቲት ጋር በመተባበር ''የቅድመ አክሱም የስልጣኔ ዘመን እና የምሁራን ምልከታ'' በሚል ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በአክሱም ከተማ ተካሄዷል። የጀርመን አርኪዮሎጂ ኢንሰቲዩቲት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሳራ ጃፕ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት፣ ከተለያዩ  ሃገራት የመጡ የዘርፉ ምሁራን በቅድመ አክሱም ጥንታዊ ህንጻዎችና የአርኪዮሎጂ ስፍራዎች ተጨማሪ የጥናትና ምርምር ስራዎች እያካሄዱ ይገኛሉ። ''ማይ አድራሻ፣ ይሓ፣ ቤት ገርግስና ቤት ሰማእቲ'' የመሳሰሉ የቅድመ አክሱም ስፍራዎች ያሉ ቅሪተ አካላት ለስራው እንደ ጠቃሚ ግብአት በመጠቀም  ምርምር እየተካሄደባቸው ነው ብለዋል። ምሁራኑ በጥንታዊ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ ስልጣኔዎች ጥናትና ምርምር ላይ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ተጨማሪ ስራዎች እንደሚጠበቁ ዶክተር ሳራ ተናግረዋል። በይሓና አከባቢው በድንጋይ እና እንጨት የተሰሩ ጥንታዊ ቤቶችና የማህበረሰቡ መገልገያ ቁሳቁሶች በምርምር የተገኙ ናቸው። በሙዚየም ውስጥ ተቀምጠው ለቱሪዝም ልማት ተጨማሪ ሃብት መሆናቸውን ጠቁመዋል። "ዛሬም የይሓ ጥንታዊ ከተማ ዋነኛ የአለም አቀፍ የአርኪዮሎጂ ምሁራንን ጥናትና ምርምር ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ነው "ብለዋል። በኢጣሊያ ኔፕልስ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂ ምሁር የሆኑት ዶክተር ሉሺያ ሰርኒኮላ በቅድመ አክሱም ቅሪተ አካል ላይ ባተኮሩ 30 ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ ምርምር ማካሄዳቸውን ገልጸዋል። በቅድመ አክሱም ስማቸው የማይታወቅ ማህበረሰብ እንደነበር ጠቅሰው ''ቤት ሰማእቲ፣ ይሓ እና ማይ አድራሻ'' በምርምር በተገኙ ቅሪተ አካል ላይ የጣሊያን ምሁራን መሳተፋቸውን አስረድተዋል። በቀጣይም በስፍራዎቹ በሚደረጉ የአርኪዮሎጂ ጥናትና ምርምር ስራዎች ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እንደሚሰሩ አስታውቀዋል። ዶክተር ሉሺያ በቅድመ አክሱምና በአክሱም ዘመን የነበረ ስልጣኔ ላይ ይበልጥ ጥናት ለማድረግ ግብአት የሚሆኑ ሐውልቶች፣ መቃብር ስፍራዎችና የአርኪዮሎጂ ቦታዎች አሁን ጉዳት እየደረሰባቸው በመሆኑ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባም አሳስበዋል። ''የቅድመ አክሱም እና የዘመነ አክሱም የጥበብና ታሪክ ስልጣኔ አዲሱ ትውልድ እንዲጋራውና እንዲያውቀው የዘርፉ ምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው'' ያሉት ደግሞ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር መርሃዊ አብርሃ ናቸው። የጀርመን አርኪዮሎጂ ኢንስቲትዩት እና የጣልያኑ ኔፕልስ ዩኒቨርሲቲ ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቅደመ አክሱም ስልጣኔ በነበሩ ጥንታዊና ታሪካዊ ስፍራዎች ላይ ውጤታማ ምርምር እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል። የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራንም ከሁለቱ ተቋማት በቴክኖሎጂ ሽግግርና ሰው ኃይል ልማት ተጨማሪ እውቀትና ልምድ እያገኙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ገና ያልተጠኑ የቀደምት ስልጣኔ መገለጫ የሆኑ ታሪካዊ ቅርሶች በጥናትና ምርምር በመለየትና በመሰነድ ለአለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ የዘርፉ ምሁራን ሚና ትልቅ መሆኑንም ዶክተር መርሃዊ ተናግረዋል። የአክሱም የቀደምት ስልጣኔ መነሻዎችና መገለጫዎች በአግባቡ ለማወቅ ተጨማሪ  የጥናትና ምርምር ስራዎችን እንደሚጠይቁ  የገለጹት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ተክላይ ሓጎሰ ናቸው። በውይይት መድረኩ  ከተለያዩ የዓለም ሀገራት እና ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ ከ100 በላይ የዘርፉ ምሁራን ተሳትፈዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም