ስለ አማራ ሕዝብ ማንነት የተፈጠሩ የተሳሳቱና የተዛቡ ታሪኮች ኅብረ ብሄራዊ አንድነት እንዳይፈጠር እንቅፋት ሆነዋል

157

አዲስ አበባ የካቲት 14/2012 (ኢዜአ) በአማራ ሕዝብ ማንነት ላይ የተፈጠሩ የተሳሳቱና የተዛቡ ታሪኮች የኢትዮጵያን ኅብረ ብሄራዊ አንድነት ለመገንባት እንቅፋት በመሆናቸው ሊታረሙ እንደሚገባ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በይነ መንግስታት ቢሮ አሳሰበ።

ይህን ትርክት ለማረም የክልሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ምሁራንና አክቲቪስቶች እውነተኛውን የአማራ ህዝብ ማንነት በማሳየት ከሌሎች ብሄሮች ጋር በሚያስተሳስሩት እሴቶች ላይ እንዲሰሩም መልዕክት ተላልፏል።

ቢሮው “የአማራ አብሮነት እሴቶች ለህብረ ብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ብሄሩን መሰረት ያደረጉ የተሳሳቱ ትርክቶችን ማረም ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂዷል።

የአማራ ህዝብ ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር በመሆን በአገር ሉዓላዊነት ማስከበርና ግንባታ፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በማስወገድ ረገድ ጉልህ ሚና የነበረው መሆኑም በውይይቱ ተነስቷል።

ለዚህም ለውጡን ተከትሎ ችግሮች ሲፈጠሩ በአማራ ክልል የሚገኙ ሌሎች ብሄረሰቦች ችግር ውስጥ አለመውደቃቸው ለህዝቡ አብሮ የመኖር እሴትና የአንድነት ስሜት ማሳያ ነው ሲሉ የበይነ መንግስታቱ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ታደሰ ተስፋው ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ላለፉት ዓመታት ይህን እውነተኛ ታሪክ በማዛባት፣ የሃሰት ታሪክ በመፍጠር ሌላው የአገሪቷ ማህበረሰብ በአማራ ህዝብ ላይ ጥላቻ እንዲያሳድር መደረጉን ገልጸዋል።

ይህም በአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር እየተካሄደ ያለውን የጠንካራ ህብረ ብሄራዊ አንድነት ግንባታ የሚያሰናክል ስለሆነ ሊታረም ይገባል ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ይህ የተሳሳተ የማንነት ታሪክ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲባል ታስቦበት የተፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።

ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እውነተኛውን የአማራን ህዝብ እሴት በማሳየት የተሳሳተውን ትርክት ለማረም መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በተለይም የፖለቲካ ድርጅቶች ከመከፋፈል ይልቅ በአንድ ላይ በመደራጀት በአገራዊ አንድነትና አብሮነት ላይ ቢሰሩ ችግሩን ማቃለል እንደሚቻል ገልፀዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት የሱማሌ ክልል ተወላጅ በበኩላቸው በአማራ ላይ ሲሰራ የነበረው የተዛባ ታሪክ ተጨባጭነት የሌለውና ህዝቡንም እንደማይገልፅ ተናግረዋል።

ክልሉም ይሁን የክልሉ ፖለቲከኞች ከሌሎች የአገሪቷ ብሄሮች ጋር የጀመሩትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አጠናክረው ከቀጠሉ ችግሩን ማስወገድና ለአንድነት በጋራ መስራት ይቻላልም ብለዋል።