124ኛው የአደዋ ድል መታሰቢያ በዓል በወረኢሉ ተከበረ

92

ደሴ፣ የካቲት 14/2012(ኢዜአ) 124ኛው የአደዋ ድል መታሰቢያ በዓል “ክተት ለሰላም በወረኢሉ” በሚል መሪ ሀሰብ ዛሬ በወረኢሉ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ።

የደቡብ ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ሱለይማን እሸቱ በበዓሉ ስነ ስርዓት ወቅት እንዳሉት የአደዋ ድል የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካውያን ኩራት ነው፡፡

“የጥንት ኢትዮጵያውያን በዘመናዊ የጦር መሳሪያ የተደራጀውን ወራሪ ጠላት በድል የተወጡት በዘርና በኃይማኖት ሳይከፋፋሉ ለሃገራቸው ኩራት በጋራ በመቆማቸው ነው” ብለዋል።

የአሁኑ ወቅት ትውልድም የአባቶቹን ድል አድራጊነት ወኔ በመላበስ ለዘላቂ ሰላምና አንድነት በጋራ ሊሰራው እንደሚገባው መክረዋል።

“ወሎ ለአደዋ ድል መነሻ ታሪካዊ ቦታዎች አሏት፤ የክተት ጥሪ የቀረበበት ወረኢሉና የጦርነቱ መነሻ የውጫሌ ስምምነት ይስማ ንጉስ ተጠቃሽ ናቸው” ብለዋል፡፡

አካባቢው ታሪካዊነቱን እንደያዘ ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የውጫሌው ይስማ ንጉስ ሙዚየም  እየተጠናቀቀ መሆኑንና  በወረኢሉም ተጨማሪ ሙዚየም ለመገንባት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደሪ ተወካይ አቶ እጅጉ መላኬ በበኩላቸው ትክክለኛውን ታሪክ ትውልዱ ተረድቶ የአካባቢውን ሰላም በጋራ መጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡

አንድነት የሁሉም መሰረት እንደሆነ ያመለከቱት አቶ እጅጉ በዘመናዊ መሳሪያ ታጅቦ የመጣውን የጣሊያን ወራሪ ኃይል አንድ በመሆናቸው ማንበርከክ እንዳልቻሉ አውስተዋል፡፡

የወሎ ዩንቨርሲቲ ቢዝነስና አለም አቀፍ ግንኙነት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አፀደ ተፈራ በወሎ አካባቢ ያሉ ታሪካዊ ቦታዎችን በጥናት በመለየት ለትውልዱ ለማስተላለፍ ተቋማቸው የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጸዋል።

አደዋ የኢትዮጵያውያን የአብሮነት ኃይል ከማሳየቱም ባለፈ የአፍሪካዊያን ኩራትና ድል ነው ብለዋል፡፡

ዶክተር አፀደ  እንዳመለከቱት ወጣቱ  አንድ ሆኖ ድህነትና ኋላ ቀርነት በስራ ድል በማድረግ አባቶቹን አኩሪ ታሪክ ሊደግም ይገባል።

የአባቶቻችን ጀግንነትን፣ አብሮነትን፣  ፍቅርና መከባበርን እንጂ ዘረኝነትን አላወረሱንም ያሉት ደግሞ የዓሉ ተሳታፊ ሃምሳ አለቃ መስፍን ታረቀኝ ናቸው፡፡

በዓሉ በታሪካዊ ቦታ ወረኢሉ መከበሩም ትውልዱ ታሪኩን እዲያውቅና አብሮነቱን እንዲያስቀጥል የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወጣት ሰሚር አሊ በበኩሉ “ትክክለኛውን ታሪክ ከአባቶች ተረድተን የሀገራችን ዳር ድንበርና ሰላም ለመጠበቅ የድርሻችንን እንወጣለን፤ ከአደዋም ብዙ ተምረናል” ብሏል፡፡

በዓሉ  በፈረስ ግልቢያ፣ በሽለላ፣ ቀርርቶና ሌሎችም ደማቅ ዝግጅቶች ታጅቦ የተከበረ ሲሆን የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ አባቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና አርበኞች ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።