የምርምር ውጤቶቸን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የፋይናንስ እጥረት አጋጠመው

88

ባህር ዳር፣ የካቲት 14/2012 (ኢዜአ) በዩኒቨርሲቲዎች የሚወጡ የምርምር ውጤቶችን አባዝቶ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የፋይናንስ እጥረት ማጋጠሙ ተገለጸ።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው  ዓመታዊ ዘርፈ ብዙ የሳይንስ ምርምር የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ኬሚስትሪ መምህር ፕሮፌሰር ሽመልስ አድማሴ ባቀረቡት የመወያያ ጹሁፍ ላይ እንዳሉት በርካታ ችግር ፈቺ ምርምሮች በዩኒቨርሲቲዎች እየተከናወኑ ነው።

የህብረተሰቡን ችግር ሊያቃልሉ የሚችሉ የተለያዩ የምርምር ውጤቶች ብዙ ከተደከመባቸው በኋላ ከመደርደሪያ ያለፈ ተግባር ላይ እየዋሉ አይደለም።

የሚወጡ  የምርምር ውጤቶች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ባለደርሻ አካላት በተለይም የክልል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ወደ ህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ የፋይናንስ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።

በየክልሎች የሚገኙ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር መመሪያ ያላቸው ቢሆንም ከሃሳብ የዘለለ ተግባራዊ እንዳልተደረገ ፕሮፌሰር ሽመልስ  በጹሁፋቸው አመላክተዋል።

የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ችግር ፈች ምርምሮች እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆኑ የመተርጎምና አቅጣጫን የማሳየት ስራ ያከናውናሉ።

ይህም በወረቀት ላይ እንጂ ወደ ማህበረሰቡ ለማውረድ የገንዘብ ችግር ስለሚያጋጥም የምርምር ውጤቶቹ  በዩኒቨርሲቲው ውስጥ መነጋገሪያ ብቻ ሁነው እየቀሩ ነው።

የመድረኩ ዓላማ በዩኒቨርሲቲዎች የሚወጡ  የምርምር ውጤቶች  ወደ ማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ  በሚቻልበት ዙሪያ  በጋራ ለመምከር እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ  የሳይንስ ኮሌጅ የድህረ-ምረቃ  ምርምር ማህበረሰብ አግልግሎት ምክትል ዲን  ዶክተር  ፀጋየ ካሣ ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው  ችግር ፈች የውሃ ማከሚያ ኬሚካሎችንና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በምርምር ማግኘት ቢችልም  ወደ ተጠቃሚው ማህበረሰብ ለማውረድ የገንዘብ እጥረትና የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ትስስር ችግር ማጋጠሙን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና  ኢንፎርሜሽን  ኮሙዩኒኬሽን  ኮሚሽነር ዶክተር ሰብስበው አጥቃው በበኩላቸው ምርምሮችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል በጀት እንደ ክልል እንደማይመደብ አስረድተዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች የሚወጡ  የምርምር ውጤቶች ከርዕስ ጀምሮ የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት አቅጣጫ በማስቀመጥ በኩል ችግር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የክልሉን ህዝብ ችግር መሰረተ ያደረጉ የምርምር ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ምርምሮችን በገንዘብ በማገዝ ወደ ህብረተሰቡ እንዲወርዱ በማድረግ በኩል እንደ ክልል ውስንነት አለ ብለዋል።

አሁን ግን የራሱ የሆነ በጀት እንዲኖረው "ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትረስት ፈንድ" የሚል ጥናት ተዘጋጅቶ ለክልሉ መንግስት መቅረቡን አስታውቀዋል።

የክልሉ መንግስትም ያጸድቀዋል ብለው እንደሚጠብቁ ጠቁመው በቀጣይ ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ፈች ምርምሮችን እየሰሩ ካቀረቡ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል "ብለዋል።

ለሁለት ቀን በሚቆየው የምክክር መድረኩ ከባህርዳር፣ አዲስ አባባ፣ የደብረ ብረሃን፣ወሎና ደብረተቦር ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ምሁራን እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም