የህዝብን አብሮ የመኖር እሴት ያጎድፋል የተባለ መጽሐፍ ሊወገድ ነው

74
አርባምንጭ ሰኔ 20/2010 በጋሞ ጎፋና አጎራባች ዞኖች የሚኖሩ ብሔረሰቦችን አብሮ የመኖር እሴት ይሸረሽራል የተባለ መጽሐፍ እንዲወገድ መወሰኑን የጋሞ ጎፋ ዞን ፍትህ መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያ ኃላፊው አቶ ጌትነት ስንታዬሁ ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት እንዲወገድ የተወሰነው "ማላና ዶጋላ ህዝቦች ታሪክ" በሚል ርዕስ ከሶስት ዓመታት በፊት ታትሞ የተሰራጨው "ማዶላ" የተሰኘው መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ የያዘው  መልዕክት ተገቢ ባለመሆኑና የትኛውንም ብሔረሰብ የማይወክል በመሆኑ ህብረተሰቡ እንዲወገድ ሲጠይቅ መቆየቱን ተናግረዋል። የዞኑ ፍትህ መምሪያም መጽሐፉ እንዲወገድና ጸሐፊውና ተባባሪዎቹ እንዲጠየቁ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሰረተው ክስ መሰረት ትላንት የዋለው 13ኛው ምድብ ተዘዋዋሪ ችሎት መጽሐፉ ተሰብስቦ እንዲወገድ ወስኗል። ከዚህም ሌላ መጽሐፉ ከሰኔ 19/2010 ዓ ም ጀምሮ በየትኛውም ህትመት ውጤቶች ላይ በማጣቀሻነት እንዳይቀርብና ጥቅም ላይ እንዳይውል ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አካቷል። መጽሐፉን በመጻፍ፣ በማሳተምና በማሰራጨት ክስ ከተመሠረተባቸው መካከል የመጽሐፋ ደራሲ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቱ ክሱ መቋረጡን ገልጸው፤ ያሳተመው ድርጅትም አሰቀድሞ በተሰጠ ውሳኔ መቀጣቱን ተናግረዋል። የመጽሐፉ ቅጂዎች ሰርጭት ከሶስት ዓመታት በፊት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰብሰባቸውንና በአሁኑ ጊዜ በጋሞ ጎፋ ዞን ፖሊስ ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ገልጸዋል። የተሰበሰቡት የመጽሐፉ ቅጅዎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮችና የከተማ ነዋሪዎች በተገኙበት የፊታችን ሰኞ ሰኔ 25/2010 ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ በህዝብ ፊት እንደሚቃጠል አቶ ጌትነት ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም