በምርጫው ለመሳተፍ አዳጋች ሁኔታዎች እየገጠሙኝ ነው - ትዴፓ

87
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 13/2012 የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ /ትዴፓ/ በመጪው አገራዊ ምርጫ በትግራይ ክልል በዴሞከራሲያዊ መንገድ መወዳደር የሚያስችል እንቅስቃሴ ለማድረግ ተቸግሬያለሁ አለ፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ለኢዜአ እንደገለፁት ፓርቲያቸው በመጪው አገራዊ ምርጫ በክልል ደረጃ ተወዳድሮ ለማሸነፍ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። ነገር ግን በአካባቢው ከሚንቀሳቀሰው ህወሃት የተለያዩ ችግሮች እየገጠማቸው መሆኑን ተናግረዋል። ፓርቲው በክልሉ በመቀሌ ብቻ ቅርንጫፍ መክፈቱን የገለጹት ዶክተር አረጋዊ ፤ በአብይአዲ፣ በሽሬና በአድዋ ቅርንጫፎች ለመክፈት ሙከራ ማድረጉንም ጠቅሰዋል። ይሁንና በትግራይ ክልል ነጻና ፍትሃዊ የምርጫ እንቅስቃሴ ለማድረግ መቸገሩንና አባላቱም ለእስራት፣ ለድብደባና ለእንግልት እየተዳረጉ መሆኑን ጠቁመዋል። "ይህ ባለበትና ምርጫ ቦርድ ባለሙያዎች ባልመደበበት ሁኔታ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ምርጫ ለማከናወን ማቀዱ ተገቢ አይደለም'' ነው ያሉት። ችግሩን በተመለከተ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ለምርጫ ቦርድና ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በደብዳቤ በማሳወቅ ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑንም ዶክተር አረጋዊ አስረድተዋል። የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ መስፍን ደሳለኝ በበኩላቸው ፓርቲያቸው በክልሉ በምርጫ ተሳታፊ ለመሆን በመንግስትና በምርጫ ቦርድ ዋስትና ሊያገኝ እንደሚገባ አመልክተዋል። ስለ ጉዳዩ የትግራይ ክልል የስራ ሃላፊዎችን በስልክ ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ ስለሁኔታው ተጠይቀው ቦርዱ በትግራይ ክልል ሰው አልመደበም መባሉ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመው ፤ በመቀሌ ቅርንጫፉን ከፍቶ አስተባባሪ መመደቡን ተናግረዋል። ፓርቲው ለቦርዱ ያቀረበው ቅሬታም ካለ እንደሚታይም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም