መጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ለመግታት የጋራ ርብርብ ተጠየቀ

330
አዳማ ኢዜአ የካቲት 13/2012 መጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በወጣቶች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደሩ በመምጣታቸው በጋራ ርብርብ ሊገቱ ይገባል ሲል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አሳሰበ ። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወጣቱን የመጤ ባህሎችና አደንዛዥ እፅ ተጋላጭነት ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዳማ ከተማ መክሯል ። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሠረት እንደገለጸት መጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በወጣቶች ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። የወጣቶች ስነ ልቦና፣ማህበራዊ ግኑኝነቶችና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን በማዳከም ማንነትን የሚያበላሽ ተግባር መሆኑን ገልጠዋል። በአሁኑ ወቅት ከማህበረሰብ ባህልና አስተሳሰብ ጋር አብረው የማይሄዱና የማይዛመዱ ነባሩ የህብረተሰቡን ባህል የሚጎዱ መጤ ባህሎች እየተስፋፉና እየተላመዱ መምጣታቸውንም አመልክተዋል። አሁን ላይ በከተሞችና አልፎ አልፎ በገጠራማ የሀገሪቷ አካባቢዎች ሳይቀር በወጣቶች ደረጃ እየተስፋፋ የመጣውን መጤ ባህልና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመግታት የተቀናጀ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ወይዘሮ ብዙነሽ አስገዝበዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ነባር ባህል እንዳይበረዝና እንዳይጠፋ ከሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር፣ከምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። ሀገሩንና ባህሉን የሚወድና የሚጠብቅ ዜጋ ለመገንባት የባህል እሴቶች ልማት ላይ በትኩረት መስራት አለብን ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታዋ በዚህም ሀገር በቀል ባህሎችን ማጥናት፣ማልማትና ለዓለም ማህበረሰብ ማሳወቅ ይጠበቅብናል ብለዋል። የከተሜነት መስፋፋትና ዕድገት ጋር ተዳምሮ የመጤ ባህሎችና የአደንዛዥ ዕፆች ዝውውር እየጨመረ በመምጣቱ በወጣቶችና ታዳጊዎች ስብዕና ግንባታ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑንም ገልጠዋል። በዚህም የህዝቡ ማህበራዊና ባህላዊ ትስስር እንዲላላ፣የእምነት ሥርዓቶች እንዳይከበሩ፣ሀገር በቀል እውቀቶች እንዲዳከሙና የባህል እሴቶቻችን ለትውልድ ማስተላለፍ በማንችልበት ደረጃ ላይ እንድንገኝ እያደረገን ነው ብለዋል ። ይህን ድርጊት መከላከል ከቤሰተብ መጀመር አለበት ያሉት ወይዘሮ ብዙነሽ ልጆች መልካምና መጥፎውን ለይተው እንዲያውቁ ማስተማር ይገባናል ነው ያሉት። በተጨማሪም በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሀገር በቀል የባህል እሴቶች እንዲስፋፉና እንዲለሙ በትብብር መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል። የመድረኩ ዓላማ አሉታዊ መጤ ባህሎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የተቀረፀውን ስትራቴጂ ውጤታማ ለማድረግ የተቋቋመውን ግብረሃይል ወደ ሥራ ለማስገባት እንደሆነም አመልክተዋል። ድርጊቶቹ ለትዳር መፍረስ፣ቤተሰብ እንዲበተን፣ ታዳጊዎችና ወጣቶች ወደ ጎዳና እንዲወጡ ምክንያት እየሆኑ ናቸው ያሉት ደግሞ በመድረኩ ላይ ፅሑፍ ያቀረቡት በሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ስብዕና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰይድ ዓለሙ ናቸው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ጨምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ጭምር ለችግሩ እየተጋለጡ መሆኑን ገልጠዋል። ተማሪዎቹ ለስነ ልቦናና አካላዊ ጥቃቶች ከመዳረግ ባለፈ የቁማር ሱስ፣ለአልኮል መጠጥ፣ለትንባሆ ፣አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነትና ለስርቆት ወንጀል የሚደረጉበት ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው ብለዋል። የትውልድን አውንታዊ እድገት የሚገቱ መጤ ባህሎችና ድርጊቶችን ለማስቀረት ሁሉም በወጣቶች ክህሎት፣ግንዛቤና አስተሳሰብ ለውጥ ዙርያ  በቅንጅት መስራት ይጠበቅብናል የሚል መልእክት አስተላልፈዋል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም