የሽሬ እንዳስላሴ ማዘጋጃ ቤት የተንዛዛ አሰራሩን አስተካክሏል

57
የሽረ እንዳስላሴ፣ የካቲት 13/2012 (ኢዜአ) የሽረ እንዳስላሴ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የተንዛዛ አሰራሩን በማስተካከል ተገልጋዮችን በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ አስተናግዶ በመሸኘት ተስፋ ሰጪ ጅምር ማሳየቱን ተገልጋዮች ገለፁ። ከሽረ እንዳስላሴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ምልእተ በየነ ለኢዜአ እንደገለጹት ከአሁን በፊት ወደ ማዘጋጃ ቤቱ  ለጉዳይ ሲሔዱ ከበር ጀምሮ  ወከባና አላስፈላጊ ምልልስ ያጋጥማቸው እንደነበር ተናግረዋል። እሳቸውን ጨምሮ በአገልግሎቱ ህብረተሰቡ ሲማረር መቆየቱን ገልፀው ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ግን የአገልግሎት አሰጣጡ በመስተካከሉ ጉዳያቸውን ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ወስጥ መጨረሳቸውን አስረድተዋል። ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ሻምበል ኪዱ ብርሃነ በበኩላቸው  ቀደም ሲል ፋይል በቀላሉ ማግኘት ቀርቶ ጠፋ እየተባለ ተገልጋዩ ለእንግልት ይዳረግ ነበር ብለዋል። አሁን ግን አሰራሩን በማስተካከሉ በርከታ ነዋሪዎች  በአገልግሎቱ እርካታ ማግኘት መጀመራቸውን ተናግረዋል። “የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ የያዘ ፋይልህ ጠፍቷል ተብየ ለዓመታት በመንከራተት ተስፋ ቆርጨ ነበር ያሉት” ደግሞ  በከተማው የ03 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ታረቀ ብርሃነ ናቸው። ማዘጋጃ ቤቱ የአገልግሎት አሰጣጡ ማዘመን ከጀመረ ወዲህ ግን ጠፋ የተባለው ፋይል ተገኝቶ ጉዳያቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ በመጨረስ  የፈለጉትን ማስረጃ በእጃቸው እንደገባ ተናግረዋል። ማዘጋጃ ቤቱ የጀመረው ተስፋ ሰጪ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ባለ ድርሻ አካላትና የነዋሪው ህዝብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል። የማዘጋጃ ቤቱ ስራአስኪያጅ አቶ ፀጋይ ገብረሚካኤል በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት አገልግሎት አሰጣጡ ፈጣንና ተደራሽ የሆነው ላለፉት ሁለት ወራት አዲስ የአሰራር ሪፎርም ስራ እንዲውል በመደረጉ ነው። ሪፎርሙ የማዘጋጃ ቤቱ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በማዘመን የተገልጋዩን ህብረተሰብ ፍላጎት ለማርካት ያለመ በመሆኑ ተጨባጭ ውጤት ማሳየት መጀመሩን አስረድተዋል ። ተገልጋዩ እንደ አመጣጡ ሳይዋከብ እንዲገለገልና ወደሚፈልገው ክፍል በመጠቆም ጊዜ ቆጣቢ አገልግሎት እንዲያገኝ የመረጃ ዴስክ ተቋቁሞ ተገቢው ስራ እያከናወነ ነው ብሏል። ከአሁን በፊት ሁሉም የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች በዋናው ጽህፈት ቤት ይሰጥ የነበረው አሁን ከፊል የማዘጋጃ ቤቱ አገልግሎት በየቀበሌዎቹ በተቋቋሙት ንኡስ ቅርንጫፎች አማካኝነት እንዲያልቁ በመደረጉ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት አንዱ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ቀደም ሲል ይሰጠው በነበረው አገልግሎት ህብረተሰቡ ደስተኞ እንዳልነበረ ጠቅሰው አሁን ይህን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ቆርጦው መነሳታቸውን ተናግረዋል። የሽረ እንዳስላሴ ከተማ ከመቐለ ቀጥሎ በስፋትና በህዝብ ብዛት 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ትልቅ ከተማ ነው ተብሏል። ኢዜአ የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የተንዛዛ አሰራር ነዋሪዎችን እያማረረ መሆኑን ጠቅሶ ባለፈው ዓመትና ከሶስት ወር በፊት የዜና ዘገባዎች አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም