ሴፍትኔት ፕሮግራም እራሳቸውን ለመቻል እንደረዳቸው ተጠቃሚዎች ገለጹ

65
ሰቆጣ፣ ኢዜአ የካቲት 13/2012(ኢዜአ) በሴፍትኔት ፕሮግራም ታቅፈው የተደረገላቸው የብድር ገንዘብ አቅርቦት ድጋፍ ሰርተው እራሳቸውን ለመቻል እንደረዳቸው በዋግ ህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ተጠቃሚዎች ገለጹ። በዞኑ በፕሮግራሙ የታቀፉ 49 ሺህ ሰዎች በተመቻቸላቸው 100 ሚሊዮን ብር የብድር ገንዘብ በገቢ ማስገኛ ስራዎች ተሰማርተው  ውጤታማ በመሆን ላይ እንደሚገኙ ተመልክቷል። በብሄረሰብ አስተዳደሩ ዝቋላ ወረዳ የበሌ አንድ አርሶ አደር ጌታሁን ኪዴ ለኢዜአ እንዳሉት አስር ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደር የሚችል ገቢ ስላልነበራቸው በየዓመቱ መንግስት በሚያቀርብላቸው የእለት ደራሽ  እርዳታ ሲጠቀሙ ቆይተዋል። ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት ባመቻቸላቸው 12 ሺህ ብር የብድር ገንዘብ አምስት እናት ፍየሎችን ገዝተው ወደ እርባታው መሰማራታቸውን ተናግረዋል፡፡ "በእንስሳ እርባታው ጠንክሬ በመስራቴ የነበሩኝ ፍየሎች ቁጥር አሁን ላይ ከ30 በላይ ማድረስ ችያለሁ፤ የወሰድኩትን ብድርም በወቅቱ መልሻለሁ" ብለዋል። ከዚህም በሚየገኙት ገቢ ቀደም ሲል ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር ይገጥማቸው የነበረውን ችግር በመቃለሉ እራሳቸውን ለመቻል እንደረዳቸው ገልጸዋል። የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ቸኮሉ ነይኑ በበኩላቸው "ሶስት ልጆቼን ያለ አጋዥ አሳዳጊ በመሆኔ በሚቀርብልኝ የእለት እርዳታ ቤተሰቦቼን ለማስተዳደር እቸገር ነበር " ብለዋል። ከ2010 ዓ.ም ጀምረው በሴፍትኔት ፕሮግራም ታቅፈው በተሰጣቸው 8 ሺህ ብር ብድር  በአትክልት እና ፍራፍሬ ንግድ እንደተሰማሩ ተናግረዋል፡፡ በተሰማሩበት ንግድ ጠንክረው በመስራታቸው የወሰዱትን ብድር በመመልሰ ከሚያገኙት ገቢ 20ሺህ ብር መቆጠብ እንደቻሉ አስረድተዋል። አሁን ላይ በንግድ ከተሰማሩ ወዲህ ኑሯቸው እየተሻሻለ መምጣቱን እና ልጆቻቸውንም ትምህርታቸውን እያስተማሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የተመቻቸላቸውን የብድር ገንዘብ ተጠቅመው ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ በእንስሳት እርባታ እንደተሰማሩ የገለጹት ደግሞ በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የፀመራ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አወጡ ሞገስ ናቸው። በ8ሺህ ብር በጀመሩት የእንስሳት እርባታ ውጤታማ በመሆን ብድራቸውንም መመለሳቸውንና 33የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በብሄረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ የሴፍትኔት ፕሮግራም የኑሮ ማሻሻያ ዘርፍ ባለሙያ አቶ መኮንን አክሎ እንደገለጹት ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የሴፍትኔት ተጠቃሚዎች የቤተሰብ ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ የብድር አገልግሎቱን እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። ባለፉት አራት ዓመታት በፕሮግራሙ ለታቀፉ 49ሺህ ሰዎች  በተመቻቸላቸው 100 ሚሊዮን ብር የብድር ገንዘብ በእንስሳት እርባታ፣ ምግብ እና መጠጥ ንግድ ዘርፍ  እንዲሰማሩ መደረጉን አመልክተዋል። በዚህም የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሁለት ሺህ 356 አባውራዎች በምግብ እራሳቸውን ችለው ከሴፍትኔት ፕሮግራሙ መመረቃቸውን አስረድተዋል። ቀሪዎቹን ከፕሮግራሙ ለማስመረቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። በተያዘው ዓመትም  42 ሚሊየን ብር ብድር በማመቻቸት ከአራት ሺህ በላይ ሰዎችን በኑሮ ማሻሻያ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ከ151ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የሴፍትኔት የእለት ምግብ እርዳታ የሚደረግላቸው መሆኑም ከመምሪያ  የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም