ዩኒየኑ የገነባው የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለአገልግሎት ዝግጁ ነው

109
ጎንደር ኢዜአ 12/06/2012 በጎንደር ከተማ ጃንተከል የወተት አምራቾች ሀብረት ስራ ዩኒየን ያቋቋመው የወተት ተዋፅኦ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተከላው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ዩኒየኑ አስታወቀ ። የማእከላዊ ጎንደር ዞን ህብረት ስራ ማህበራት ተጠሪ ጽህፈት ቤት የስራ አመራር ባለሙያ አቶ እንዳለው ፀጋዬ ለኢዜአ እንደገለፁት የጃንተከል የወተት አምራቾች ህብረት ስራ ማህበር ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ያቋቋመው ፋብሪካ በቀን 10 ሺህ ሊትር ወተት የማቀነባበር አቅም ያለው ነው። ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት የህንጻ ግንባታውና የማሽነሪ ተከላ ስራው ተጠናቆ የመሳሪያ ፍተሻ የተደረገለት ሲሆን በመጪው ሚያዚያ ወር ተመርቆ የማምረት ስራ ይጀምራል፡፡ ፋብሪካው ፓስቸራይዝድ እሽግ ወተትን ጨምሮ አይብና የገበታ ቅቤ በማምረት ለጎንደር ከተማና አካባቢው የሚያቀርብ ነው ተብሏል። ፋብሪካው ወደ ምርት ስራ ሲገባ ለ20 ወገኖች የስራ እድል እንደሚፈጥር ባለሙያው ገልፀዋል። ማቀነባበሪያ ፋብሪካው ጎንደር ከተማን ጨምሮ በአምስት ወረዳዎች ከሚገኙ አባላቱ የወተት ምርት በመረከብ አስተማማኝ ገበያ የሚፈጥር ነው። የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር መልኬ ታድሎ በሰጡት አስተያየት ከሁለት የውጪ ዝርያ ያላቸው ላሞች የሚያገኙትን ወተት በዩንየኑ አማካኝነት ለማቀናባበሪያ ፋብሪካው ለማስረከብ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ በጾም ወራቶች የወተት ገበያ ስለሚቀዛቀዝ የወተት ምርታቸው ይባክን እንደነበር የገለጹት ደግሞ የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሞገስ ታዬ ናቸው፡፡ የፋብሪካው መቋቋም ሰፊ የገበያ እድል ይዞ የመጣ ከመሆኑም በላይ በተመጣጣኝ ዋጋ የወተት ምርታቸውን በመሸጥ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው በመሆኑ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ ጃንተከል የወተት አምራቾች ህብረት ስራ ዩንየን 660 አባላት ያሉት ሲሆን 10 ሚሊዮን ብር ቋሚና ተንተቀሳቃሽ ካፒታል እንዳለውም ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም