የዕንባ ጠባቂ ተቋሙ የመፍትሔ ሃሳቦች በአመራር አካላት ዳተኝነትና ትኩረት ማነስ ምላሽ እያጡ ነው

99

  አዲስ  አበባ የካቲት 13/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚያቀርባቸው የመፍትሔ ሀሳቦች ምላሽ የሚያጡት በታችኛውና በመካከለኛው የመንግስት አስተዳደር እርከን አመራሮች ዳተኝነትና ትኩረት ማነስ ነው ተባለ።

አዋጅ ቁጥር 1142/2011 አንቀጽ 35 ዕንባ ጠባቂ ተቋም ስልጣንና ተግባሩን ስራ ላይ ማዋል እንዲችል ማንኛውም ሰው አስፈላጊውን ድጋፍ የመስጠትና የመተባበር ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል።

ተባባሪ የማይሆኑ የመንግስት ባለስልጣናት ተጠያቂነት እንዳላበቸውም ጠቅሷል።

ማንኛውም ሰው ያለ በቂ ምክንያት በተቋሙ በቀረበ የምርመራ ውጤት፣ መፍትሔ ወይም የቁጥጥር ውጤት መሰረት በ30 ቀናት ውስጥ የእርምት እርምጃ ያልወሰደ እንደሆነም ከ5 እስከ 7 ዓመት በሚደርስ አስራት ወይም 10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ፤ ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣም በአዋጁ ተመልክቷል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የስራ ኃላፊዎች የመፍትሄ ሀሳቦች ተገቢ ምላሽ የማያገኙት በአመራሮች ዳተኝነትና ትኩረት ማነስ ነው ይላሉ።

የተቋሙ የመቀሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዕንባ ጠባቂ አቶ ገብረእግዚአብሔር ገብረሚካኤል እንደሚሉት የመሬት ካሳ ክፍያና የሠራተኞች ቅጥርና ዕድገት በክልሉ ዋነኛ የአቤቱታ ምንጮች ናቸው።

በአብዛኞቹ የክልሉ ወረዳዎችም በእነዚህ ጉዳዮች ለሚቀርቡ አቤቱታዎች ከተቋሙ የሚሰጡ የመፍትሄ ሀሳቦች በፍጥነት ያለመፈጸም ችግሮች እንዳሉ ተናግረዋል።

“የመፍትሄ ሀሳቦች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ሲቀርቡ ‘ጊዜ ስጡን፣ በጀት ያንሰናል’ የሚሉ ምክንያቶችን በማቅረብ ላለመፈጸም ዳተኝነት ይታያል” ብለዋል አቶ ገብረእግዚአብሔር።

የመፍትሄ ሀሳቦች በቶሎ ባለፈጸማቸው ምክንያትም ዜጎች ቅሬታቸውን እንደሚያሰሙ ጠቅሰዋል።

ችግሩን ለመፍታት በመጀመሪያ የመፍትሄ ሀሳቦች እንዲፈጸሙ ማሳሰብ፤ በዚህ መፍትሔ የማይገኝ ሲሆን በመገናኛ ብዙሃን የማጋለጥ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ነው አቶ ገብረእግዚአብሔር የሚናገሩት።

አመራሮች በሁለቱ አማራጮች እምቢተኝነት ካሳዩ በፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ እንዲከሰሱ እንደሚደረግ የገለጹት አቶ ገብረእግዚአብሔር በክሱ ቅጣት እንዳይመጣባቸው ሲሉ ‘የመፍትሔ ሀሳቦችን ወደመፈጸም እየገቡ ነው’ ብለዋል።

እነዚህ አካላት ለመፍትሄ ሀሳቦች ፈጣን ምላሽ የማይሰጡት የተቋሙን ተግባርና ሃላፊነት በውል ካለመረዳት እንደሆነ በመገንዘብ በጽህፈት ቤቱ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

“የመፍትሔ ሀሳቦችን ተቀብለው የሚያስፈጽሙ እንዳሉ ሁሉ ባላቸው ግትር አቋም የሚመጡ ጉዳዮችን አናስፈጽምም የሚሉ አመራሮች አሉ” ያሉት ደግሞ የተቋሙ የሃዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የምርመራ ዳይሬክተር አቶ ስምኦን አልዳዳ ናቸው።

“እናንተ ምን አገባችሁ፤ ይሄ ጉዳይ አይመለከታችሁም” የሚሉና የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱን ባለሙያዎች ለማሳሰር የሞከሩ አመራሮች እንደነበሩም ጠቁመዋል።

በአንዳንድ አመራሮች ላይ ስለተቋሙ የአመለካከት ችግር እንደሚታይና አንዳንዴም የመፍትሔ ሀሳቦችን የማስፈጸሙ ሁኔታ ከአመራሮቹ አቅም በላይ የሚሆንበት አጋጣሚ እንዳለ ተናግረዋል።

የመፍትሄ ሀሳቦች ምላሽ ባለማግኘታቸው ክስ ተመስርቶ በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙ ጉዳዮች እንዳሉም አክለዋል።

የባህርዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የምርምራ ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታደሰ ደግሞ የመፍትሄ ሀሳቦች ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ ከአስፈጻሚ አካላት ጋር በመወያየት አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከአስፈጻሚ አካላት ጋር ተቀራርቦ መስራቱ ‘የመፍትሄ ሀሳቦች በሚፈለገው ፍጥነት እልባት እንዲያገኙ ያስችላል’ ብለዋል።

አንዳንድ ጊዜ በተቋሙ ባለሙያዎች በሚቀርቡ የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ የጥራት ችግር መኖሩ በቶሎ እንዳይፈጸሙ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።

ስለዚህም የመፍትሄ ሀሳቦችን የጥራት ደረጃ መፈተሽና የባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የካቲት 9 እና 10 ቀን 2012 ዓ.ም በአዳማ ባካሄደው የ6 ወር የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ለሚያቀርባቸው የመፍትሄ ሀሳቦች በታችኛውና በመካከለኛው የመንግስት አስተዳደር እርከኖች ያሉ አመራሮች ተገቢውን ምላሽ እንደማይሰጡ ገልጾ ነበር።

በአመራር አባላቱ ዘንድ የመፍትሄ ሀሳቦችን የማስፈጸም ቁርጠኝነት ችግር በመኖሩ እርምጃ የማይወስዱ አካላትን በመክሰስ እንዲቀጡ እየደረገ እንደሆነም ገልጿል።

በፌዴራል መንግስት ተቋማት ለመፍትሄ ሀሳቦች ምላሽ የመስጠት ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እየታየ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይህም ቀጣይነት እንዲኖረው ተጠይቋል።