የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ነገ ይካሄዳል

122

  አዲስ  አበባ የካቲት 13/2012 (ኢዜአ) የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ነገ ይፈጸማል፤ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አንዳንድ አገሮች ሥምምነቱ ዳግም እንዳይጣስ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ደቡብ ሱዳን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2013 ነበር ወደ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ የገባችው።

ለግጭቱም ዋነኛ መንስኤ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ምክትላቸውን ሪክ ማቻር ‘ከሥልጣን ሊያወርደኝ አሲሮብኛል' በሚል ከሌሎች የካቢኔ አባላት ጋር ከሥልጣን ስላስነሷቸው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ነጻነቷን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2011 የተጎናጸፈችው አዲሲቷ የአፍሪካ አገር ወደ ለየለት የእርስ በርስ ግጭት በመግባት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሰብዓዊ ቀውስ ገባች።

ግጭቱ የብሔር መልክ እየያዘ በተቃዋሚው ሪክ ማቻርና በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር መካከል ያለው የሥልጣን ቁርሾ ለበርካቶች ደቡብ ሱዳናውያን ሞትና ስደት ምክንያት ሆኗል።

በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) እና በኢትዮጵያ መንግሥት ሁለቱን ቡድኖች ለማስማማት ጥረት ቢደረግም ውጤት ማምጣት አልቻለም።

በተለይም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጣር በ2015 የተደረሰውን የሠላም ሥምምነትና የተኩስ አቁም ሥምምነቶች ሁለቱም ጎራዎች በተከታታይ በመጣስ ግጭቱን አባብሰውታል።

ይህም አገሪቱ ካላት 12 ሚሊዮን ሕዝብ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች አገራቸውን ለቀው በጎረቤት አገሮች እንዲጠለሉ አድርጓቸዋል።

ከእነዚህም መካከል 63 በመቶው የሚሆኑት ከ18 ዓመት በታች ህጻናት ናቸው።

በእርስ በርስ ግጭቱም ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች ደግሞ በአገራቸው ከቀያቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ የመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርት ያሳያል።

ያም ብቻ ሳይሆን ደቡብ ሱዳን በዚሁ የእርስ በእርስ ግጭት ከ400 ሺህ በላይ ዜጎቿንም አጥታለች።

በዚህም የደቡብ ሱዳን የሰብዓዊ ቀውስ በአፍሪካ ቀዳሚ ሲሆን በዓለም ደረጃ ደግሞ ከሶሪያና አፍጋኒስታን ቀጥሎ እጅግ አሳሳቢ የሰብዓዊ ቀውስ የሚስተዋልበት ሦስተኛ ሥፍራ በመባል ተመድቧል።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት የ2015ቱን የሠላም ሥምምነት ዳግም ተግባራዊ ለማደረግ በኢጋድ አሸማጋይነት ፕሬዚዳንቱ ሳልቫ ኪር ሥልጣናቸውን ከተቃዋሚ ጋር ለማጋራት ሌላ ስምምነት ተደርጎ ነበር።

ይህንንም የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ለማስፈጸም 100 ቀናት ቢሰጣቸውም በርካታ ጉዳዮች መፈጸም ስላቃታቸው ተጨማሪ 100 ቀናት እንዲጨመረላቸው ውሳኔ ተላልፏል።

የሁለተኛው 100 ቀናት ጭማሪ ቀነ ገደብም በነገው ዕለት ይጠናቀቃል።

ባለፈው ቅዳሜ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በአገሪቱ የነበረውን 32 የክልል አስተዳደሪዎችን ከኃላፊነታቸው በማንሳት ቀድሞ ሥምምነት በተደረገበት አስር የክልል አደረጃጃት ላይ ተስማምተዋል።

ተቃዋሚያቸው ሪክ ማቻርም ከሥምምነት መድረስ የሚቻለው ቀድሞ በነበረው 10 የክልል አደረጃጀት አልያም በ22 ክልሎች ከሆነ ብቻ መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማኅበራሰብ አሳውቀው ነበር።

አሁን ከተመሰረቱት 10 ክልሎች በተጨማሪ ሦስት የአስተዳደር ሥፍራዎች ‘ፒቦር፣ ሩዌንግና አብዬ’ በአዲሱ የመንግሥት ምሥረታ እንዲጨመሩ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ተናግረዋል።

ዛሬ ጠዋት በተደረገው መርኃ ግብርም ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በዚህ አቋማቸው መጽናታቸውን በማስመልከት መፈረማቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል።

በነገው ዕለትም ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የመጨረሻውን ሥምምነት ከተቃዋሚያቸው ሪክ ማቻር ጋር ይፈጽማሉ ተብሎ ‘በገቡት ቃል’ መሰረት ይጠበቃል።

ይህም ለአምስት ዓመታት ሲጠበቅ የነበረውን የሽግግር መንግሥት ምሥረታና የሥልጣና ማጋራት ሥምምነት የመጨረሻ እልባት ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ ደግሞ ደቡብ ሱዳን ለሰባት ዓመታት ያክል የገባችበትን የእርስ በእርስ ግጭት በመቋጨት ወደ ተረጋጋች አገር ያመራታል ተብሎ በብዙዎች ግምት ተሰጥቶታል።

ያም ሆኖ አሁንም ቢሆን የመንግሥታቱ ድርጅት፣ አሜሪካና ኖርዌይ ከሥምምነቱ በኋላ ተመልሰው ወደ እርስ በርስ ግጭት እንዳያመሩ አሳስበዋል።

አፍሪካ ኅብረትም ሁለቱ ጎራዎች ቃላቸውን አክብረው አገራቸውን ካለችበት ችግር ማውጣት እንዳለባቸው ጠንካራ ማሳሰቢያ አስተላልፏል።

አሜሪካንም ባለፈው ዓመት ሁለቱ ተቀናቃኝ ቡድኖች በአሁኑ የሠላም ሥምምነት ልዩነታቸውን አጥብበው ሥምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉ ማዕቀብ እንደምትጥል ገልጻ ነበር።

በተመሳሳይ የተባበሩት መንግሥታት ደርጅት እርምጃ ሊወስድ ይችላል የሚል ግምትም እየተሰጠ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም