በራሳቸው ተነሳሽነት ግብር የሚከፍሉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ

62

 አዲስ  አበባ የካቲት 13/2012 (ኢዜአ) በራሳቸው ተነሳሽነት ግብር የሚከፍሉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የገቢዎች ሚኒሰቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማ የላቀ የገቢ እቅድ ስኬት ማስመዝገቡንም አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ''በግማሽ ዓመት እቅዴ ስኬት እንዳስመዘግብ ረድታችሁኛል'' ላላቸው ከ350 በላይ ለሚሆኑ ከፍተኛና መካከለኛ ግብር ከፋዮች የምስጋና መርሀ ግብር አዘጋጅቶ ምስጋናውን አቅርቧል።

ሚኒስቴር በስድስት ወራት ከግብር ከፋዮች ለመሰብሰብ ካቀደው 125 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ 127 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ ከእቅዱ በላይ አሳክቷል።

ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው የተሰበሰበው በፈቃደኝነት ግብር ከከፈሉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት መሆኑ ተገልጿል።

የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ ለተመዘገበው ስኬት የግብር ከፋዮች ሚና የጎላ በመሆኑ በታማኝነት ግብር ለሚከፍሉ የማመስገን ልምድ እንዲዳብር መርሀ ግብሩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በራሳቸው ተነሳሽነት ግብር የከፈሉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ለህግ ተገዢ መሆናቸውን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

ሌሎችም የእነዚህን አረአያነት ያላቸውን ቁርጠኛ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትን ፈለግ እንዲከተሉ ጠይቀዋል።

የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን የአሰራር ስርዓቶችን በማሻሻል ዘመናዊ የታክስ አስተዳደር በመዘርጋት በ2020 ዓ.ም 3 ነጥብ 8 ትሪሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ በራስ ዓቅም በጀት የመያዝ ውጥን እንዳለ ገልጸዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር በግማሽ ዓመት ጊዜ ውስጥ የዓመት እቅዱን 52 በመቶ ማሳካት ችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም