የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ነገ ይካሄዳሉ

73
የካቲት 13/2012 (ኢዜአ) የሐበሻ ሲሚንቶ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ይካሄዳሉ። ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ፣ ጌታዘሩ ስፖርት ክለብ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችና በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈው ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ናቸው። ነገ ከጠዋቱ 2 ሰአት ከ30 በመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር ተጋጣሚዎቻቸውን ያሸነፉት ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ይገናኛሉ። ከረፋዱ 4 ሰአት ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከጌታዘሩ ስፖርት ክለብ ጋር ይጫወታሉ። ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራት ስራው ፍሬ አልባ መሆንና ተቋማት ክለቦችን ለማቋቋም ያላቸው ፍላጎት ማነስ ለሴት የቮሊቦል ክለቦች ቁጥር ማነስ ዋንኛ ምክንያቶች እንደሆነ በስፖርቱ ቤተሰቦች ይገለጻል። የሴት ቮሊቦል ክለቦች ቁጥር ማነስ የሚመለከታቸው አካላት ለሴቶች ቮሊቦል እድገት ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው የሚያመላክት ነው። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በክልልና በአዲስ አበባ ከተሞች ይካሄዳሉ። ነገ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ቡታጅራ ከተማ በሜዳው ከምባታ ዱራሜን ሲያስተናግድ፤ ጎንደር ከተማ ደግሞ ፌደራል ፖሊስን ያስተናግዳል። ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከጠዋቱ 3 ሰአት ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከሚዛን አማን ሲጫወቱ፤ ከረፋዱ 4 ሰአት ከ30 የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጋር ይጫታሉ። መቐለ ሰብዓ እንደርታና መከላከያ በሳምንቱ እረፍት የሚያደርጉ ክለቦች ናቸው። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተመሳሳይ 12 ነጥብ እርስ በርስ ሲገናኙ ባሸነፈ በሚለው ህግ በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል። መከላከያ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማና ከምባታ ዱራሜ በተመሳሳይ 10 ነጥብ እርስ በርስ ሲገናኙ ባሸነፈ በሚለው ህግ በቅደም ተከተል ከሶስት እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። አዲሱ የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ሚዛን አማን ከተማ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻው 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። በሴቶች ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ከሐዋሳ ከተማ አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ጅማ ከተማ ከወልቂጤ ከተማ በተመሳሳይ ከጠዋቱ 3 ሰአት ላይ ይጫወታሉ። በወንዶች ወልቂጤ ከተማ ከአዲሱ የሊጉ ተሳታፊ አግአዚ ውቅሮ ጋር ከጠዋቱ ሶስት ላይ ሲጫወቱ፤ ጎንደር ከተማ ከሐዋሳ ከተማ ከረፋዱ 4 ሰአት ከ30 ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም