የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የኮሮናቫይረስ የጽኑ ሕሙማን ታካሚዎች ማገገሚያ ማዕከል ለይቶ ማዘጋጀቱን አስታወቀ

55
አዲስ አበባ የካቲት 12/2012 በየቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ ጽኑ ሕሙማን ታካሚዎችን ማስተናገድ የሚችል የጽኑ ሕሙማን ማገገሚያ ማዕከል ለይቶ ማዘጋጀቱን አስታወቀ። ሆስፒታሉ የኮሮናቫይረስ ድንገት ወደ አገር ውስጥ ቢገባ በቫይረሱ የተጠቁ ጽኑ ህሙማንን ተቀብሎ እንዲያስተናግድ በጤና ሚኒስቴር መመረጡ ይታወሳል፡፡ ለዚህም ሆስፒታሉ እያደረገ ያለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ አስመልክቶ የሆስፒታሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ አምብሬ ለኢዜአ በስልክ አስታውቀዋል ፡፡ እንደዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ሆስፒታሉ ከተሟላ የሕክምና ማሽኖች ጋር አምስት ክፍሎች ያሉት የጽኑ ሕሙማን ማገገሚያ ማዕክል ለይቶ አዘጋጅቷል። በተጨማሪም በጽኑ ሕሙማን ማገገሚያ ማዕከሉ ውስጥ ለሚሰሩ 40 ሠራተኞች በኮሮናቫይረስ  ሕክምና እንዲሁም በቫይረሱ ቅድመ ጥንቃቄና መከላከያ ሥራዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች በተከታታይ በመሰጠት ላይ መሆኑን አቶ አሸናፊ አመልክተዋል። ለሆስፒታሉ ማህበረሰብ የሆስፒታሉን የክሊኒካል መዋቅር በመጠቀም ስለኮሮናቫይረስ በየዕለቱ መግለጫዎች እየተሰጠ መሆኑንም ነው የገለጹት። በቫይረሱ ዙሪያ ግንዛቤ የሚሰጡ በራሪ ወረቀቶችን በማዘጋጀት ለሠራተኞችና ለተለያየ ሕክምና ወደሆስፒታሉ የሚመጡ ታካሚዎችን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገላጻ፤ በአዲስ አበባ ለሚገኙ 13 ሆስፒታሎች እንዲሁም በኢትዮጵያ አየር መንገድና በባቡር ኬላዎች ላይ ለሚሰሩ ሠራተኞች ለቅድመ መከላከያ የሚያገለግል ቁሳቁስ ተሰራጭቷል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም