የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች እሁድና ሰኞ ይደረጋሉ

59
አዲስ አበባ የካቲት 12/2012 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር 15ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች የፊታችን እሁድና ሰኞ በሚደረጉ ግጥሚያዎች ይጠናቀቃሉ። የሊጉ የ2012 ዓ.ም የውድድር ዘመን 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው እሁድና ሰኞ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት በአዲስ አበባና በክልል ስታዲየሞች በሚደረጉ ስምንት ጨዋታዎች ነው። በመጀመሪያው ዙር ማጠናቀቂያ እሁድ ሰባት ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን ሰኞ ደግሞ አንድ ጨዋታ ይደረጋል። እሁድ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በክልል ከተሞች ሀዋሳ ከተማ ከፋሲል ከነማ፣ ድሬዳዋ ከተማ ከመቀሌ 70 እንደርታ፣ ሀዲያ ሆሳዕና ከጅማ አባ ጅፋር፣ ባህር ዳር ከተማ ከስሁል ሽረ፣ ሲዳማ ቡና ከሰበታ ከተማ እንዲሁም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከወልቂጤ ከተማ በተመሳሳይ ሰዓት ይጫወታሉ። በዚሁ ቀን በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ቅዳሜ ሊደረግ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስና የአዳማ ከተማ ጨዋታ ወደ ሰኞ ተሸጋግሯል። በመሆኑም ጨዋታው ሰኞ በአሥር ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል። በደረጃ ሰንጠረዡ መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ ውድድሩን በ27 ነጥብ አንደኛ ሆኖ ሲመራ፤ ፋሲል ከነማ በ26፣ መቀሌ 70 እንደርታ በ25 ነጥብ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው ይከተላሉ። ሲዳማ ቡና፣ ወላይታ ድቻና ስሁል ሽረ ደግሞ በተመሳሳይ 21 ነጥብ በጎል ተበላልጠው ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘው ይከተላሉ። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ደረጃ በመያዝ በሊጉ ግርጌ ስር ይገኛሉ። የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም በ13 ግቦች ሲመራ፤ አዲስ ግደይ ከሲዳማ ቡና በስምንት ግቦች፣ ፍጹም ዓለሙ ከባህር ዳር ከተማና ብሩክ በየነ ከሃዋሳ ከተማ በተመሳሳይ ሰባት ግቦች ይከተላሉ። ፍጹም ገብረማርያም ከሰበታ ከተማ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከመቀለ 70 እንደርታ፣ ባዬ ገዛኸኝ ከወላይታ ድቻ እንዲሁም ጌታነህ ከበደና አቤል ያለው ከቅዱስ ጊዮርጊስ እኩል ስድስት ግቦች አሏቸው። የሊጉ የሁለተኛው ዙር መርሃ-ግብር ውድድሮች ከሁለት ሳምንት እረፍት በኋላ ይጀመራል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም