የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምርምር የአራት ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለፀ

73
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12/2012( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምርምር ለማካሄድ የአራት ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ። በኢትዮጵያ የማህፀን ጫፍ ካንሰር አምጪ የሆነውን ቫይረስ አይነት ለማወቅና የሚደረገውን ህክምና ለመለየት የሚያስችል ምርምር ለማካሄድ ኢንስቲትዩቱ ድጋፍ ያደርጋል። ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት ሁለተኛውን አመታዊ ኮንፈረንስ እያካሄደ ሲሆን የሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስና የማህፀን ጫፍ ካንሰር የምርምር ጥምረት ቡድን አባላትም ይወያያሉ። የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ዶክተር ይርጉ ገብረህይወት በአገሪቱ በማህፀን ካንሰር ምክንያት በየአመቱ 5 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች እንደሚሞቱና ከ7 ሺህ በላይ ሰዎች በህመሙ እንደሚያዙ ገልጸዋል። በሽታውን የሚያመጣው ቫይረስ ከሁለት መቶ በላይ ዝርያ እንዳለው ተናግረው፤ ''በአውሮፓ ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ 16 ና18 ለማህፀን ካንሰር 70 በመቶ ምክንያት ናቸው'' ብለዋል። ይህንም ባማከለ መልኩም በሽታውን ለመከላከል የሚረዳ ክትባት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ የማህጸን ጫፍ አምጪ ቫይረስ የህመም መንስኤ የሆነው የትኛው ዓይነት እንደሆነ ለመለየት አገራዊ ጥናት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። በአገሪቱ ወደህክምና ከሚመጡት ሰዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ የህመሙ ደረጃ ከተባባሰ በኋላ በመሆኑ አብዛኛዎቹን ለሞት እየዳረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ''የኀብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ፣ ተደራሽነትን በማስፋትና የጤና ባለሙያዎችም ወደጤና ተቋማት ለሚመጡ ሰዎች ተገቢውን መረጃ በመስጠት ህመሙን ለመከላከል ሊተጉ ይገባል'' ብለዋል። በ2008 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ እንዳሉት፤ የባዮቴክኖሎጂ አገርአቀፍ ግብረኃይል ተደራጅቶ ሰነዶችን በመመርመር የጤና ችግሮችን የመለየት ስራ ተሰርቷል። በልየታው ከአገሪቱ ችግሮች ውስጥ የማህፀን ጫፍ ካንሰር አንዱ መሆኑ መታወቁን ገልጸዋል። የማህፀን ጫፍ ካንሰር አምጪው ሂዉማን ፓፒሎማ ቫይረስ የተለያየ ዝርያዎች ያሉት በመሆኑ በኢትዮጵያ ያለውን በመለየት ውጤታማ ህክምና ለማድረግ ኢንስቲትዩቱ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል። ''ይህም መዘጋጀቱ የሚሰጠውን ክትባት ለመወሰንና የጤና ስትራቴጂ ለመንደፍም የሚረዳ ነው'' ብለዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ ከ90 በመቶ በላይ ከ9 እስከ 14 አመት ያሉ ሴቶችን መከተብ መቻሉን የገለፁት ደግሞ የጤና ሚኒስቴር ተወካይ አቶ መንግስቱ ቦጋለ ናቸው። በአገሪቱ ለአራት አይነት የቫይረሱ ዝርያዎች የሚሆን ኳድራንት የተሰኘው ክትባት እየተሰጠ እንደሚገኝ በመጠቆም። የማህጸን ጫፍ ካንሰር በአፍሪካ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ሁለተኛው የካንሰር አይነት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። የአዲስ አበባ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ታምራት አበበ የካንሰር ቅድመ ምርመራ ማካሄድና ክትባቱን መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ አስገንዝበዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም