በቃፍታ ሁመራ ወረዳ የአንበጣ መንጋ ተከሰተ

80
ሁመራ፤ የካቲት 12/2012 (ኢዜአ) በትግራይ ምዕራባዊ ዞን በቃፍታ ሁመራ ወረዳ ልዩ ስሙ ሕለጌን በተባለው ቀበሌ የአንበጣ መንጋ ከትናንት ጀምሮ መከሰቱን የወረዳው ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በወረዳው ፅህፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ኤፍሬም ታደሰ ለኢዜአ እንደገለፁት የአንበጣ መንጋው ከጎረቤት አገራት መግባቱን ተናግረዋል። ድንበር ዘለል የሆነው ይኸው የአንበጣ መንጋ በአረንጓዴ እፅዋት ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ከአካባቢው አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጋር በመሆን የመከላከል ስራ መጀመሩን ባለሙያው ተናግረዋል ። በአከባቢው የሚገኙ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም መንጋውን በመከላከል ስራው ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አስተላልፈዋል። የአንበጣ መንጋው በተከሰተበት ቦታ ላይ ከሚገኙ አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር ስዩም ገብረስላሴ እንዳሉት የዛፍ አንበጣ መንጋው በአካባቢያቸው የተከሰተው ትናንት ከጥዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ነው ። መንጋው በተለይ የግራር ደኖችን በመብላት ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ ተናግረዋል። የአንበጣ መንጋው እየተከፋፈለ እንደሚጓዝ የተናገረው  ደግሞ ወጣት አርሶ አደር ሃይለሚካኤል ወላይ ነው። በመሆኑም የአካባቢው አየር ጸባይ መንጋውን ለመከላከል ምቹ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በቅንጅት  በመከላከል ስራው እንዲሳተፍ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም