ኢትዮጵያ የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ተቋማዊ አደረጃጀቷ በቂ አይደለም

168
አዲስ አበባ፣ የካቲት (ኡዜአ) ኢትዮጵያ በቀጣይ ሊከሰት የሚችለውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ተቋማዊ አደረጃጀቷ በቂ እንዳልሆነ የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) አስታወቀ። በኢትዮጵያ አሁን እየተደረገ ያለው የአንበጣ መከላከል ስራ ጥቂት ባለሙያዎችን በመያዝ በአንድ ዳይሬክቶሬት የሚመራ ነው። በኢትዮጵያ የፋኦ የተቀናጀ የተባይ ቁጥጥር ስርዓት ባለሙያ ዶክተር ባየህ ሙላቱ ለኢዜአ  እንዳሉት፤ በአገሪቱ እየተከሰተ ያለውን የአንበጣን መንጋ ለመከላከል በቂ ተቋማዊ አደረጃጃት ያስፈልጋል። የአንበጣ መንጋ ችግር ዘላቂ የሆነ የመከላከል ስራ እንደሚፈልግም አመልክተዋል። በግብርና ሚኒስቴር ስር በአንድ ዳይሬክቶሬት የሚመራው የአንበጣ መንጋ የመከላከል ስራ ከሚደርሰው ጉዳት አንጻር በቂ እንዳልሆነ ጠቁመዋል። ''አንበጣው በተፈጥሮው ፈጣን ምላሽና በቂ መከላከልን የሚጠይቅ ሲሆን የተደራጀ በቂ የሰው ሃይልና ሃብት ካልተመደበለት በአገር ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው'' ብለዋል። የሚመጡ ትንበያዎችን በበቂ ሁኔታ ተንትኖ ምላሽ የሚሰጥ በአገሪቱ የሚከሰቱ ተባዮችን አስቀድሞ መከላከል የሚችል ባለሙያ እንደያስፈልግም ገልጸዋል። አንበጣ ጊዜ የማይሰጥና በአጭር ጊዜ ብዙ እጽዋቶችን በመብላት ለችግር የሚዳርግ እንደሆነ የሚታወቅ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ባየህ፤ በአንድ ስኩዌር ኪሎሜትር እስከ ከ120 ሚሊዮን በላይ አንበጣ የሚፈለፈል መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ደግሞ በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ መመለስ ካልተቻለ አንድን አገር ለምግብ እህል እጦት እንደሚያጋልጥ አስረድተዋል። በኢትዮጵያ የአንበጣ መንጋ ከተለያየ አቅጣጫ በስፋት እየገባ ሲሆን ይህም ቀጣይነት እንደሚኖረው ትንበያዎች አመላክተዋል። ''አገሪቱ ካላት የቆዳ ስፋትና በተለያየ ጊዜ የሚከሰቱ ተባዮች ብዛት ችግሮችን በአንድ ዳይሬክቶሬት መምራት ውጤታማ ላያደርግ ይችላል'' ብለዋል። አገሪቱም አሁን ከታየው የአንበጣ መንጋ በላይ ቢከሰት ተቋማዊ አቅሟ ይህንን መፍታት የሚችል እንዳልሆነ ዶክተር ባየህ ጠቁመው፤ ችግሩ በጥልቀት ታይቶ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል። የአንበጣ መንጋ በቀጣይ ሶስት ዓመታት በመካካለኛው ምስራቅና በምስራቅ አፍሪካ  አገሮች ስጋት ሊሆን እንደሚችል ትንበያዎች አመልክተዋል። ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ኬሚካል መርጫ አውሮፕላን የሌላት ሲሆን አሁን እየተከሰተ ላለው የአንበጣ መንጋ ከ10 በላይ አውሮፕላን ያስፈልጋታል ነው ያሉት። ለዚህና ለሌሎችም ማሟያ የሚሆን ሃብት ያስፈልጋታል፣ ድርጅቱም ከ76 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ እየተሰራ ሲሆን የተለያዩ አካላት ድጋፍ በሰፊው ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ እስካሁን የተከሰተው በትሪሊዮን የሚቆጠር የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከል ያደረገችውን ጥረት ዶክተር ባየህ አድንቀዋል። የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ገብረእግዚአብሔር ገብረዮሀንስ እንዳሉት፤ አገሪቱ ባለፉት 10 ዓመታት የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ በራሷ አቅም መከላከል ችላለች። ''በአሁኑ ወቅት የተከሰተው መንጋ ከግብርና ሚኒስቴር አቅም በላይ ሆኖ አለም ዓቀፍ ድጋፍ እየተጠየቀ ነው'' ብለዋል። አንበጣና ሌሎች ጸረ ሰብል የሆኑ ተባዮችን ለመከላከል አገራዊ አቅምን ማጎልበት ትኩረት እንደሚሰጠው የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ''ኬሚካል ረጭቶ ማጥፋት ብቻ ሳይሆን የሌሎች ድጋፍ ሳያስፈልግ መከላከል የሚያስችል የመረጃ ስርዓት ለመዘግራት እየተሰራ ነው'' ብለዋል። በቅርቡ አንበጣ መንጋውን ለመከላከል የኢትዮጵያ አየር መንገድና ሰላም ሚኒስቴርን ያካተተ ግብረ ሃይል  እንዲዋቀር ስራ ተጀምሯል። በአንዳንድ ተቋማት ፈጣን ምላሽ ማጣት ወደ ስራ እንዳልተገባ ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም