የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማሳደግ የቴክኒክ ድጋፍ እየተደረገ ነው

60
አዲስ አበባ የካቲት 11/2012 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማሳደግ በጃፓን መንግስት የቴክኒክ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ። የኢትዮ-ጃፓን የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ልማት አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን እንዳሉት በኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማሳደግ ለተመረጡ ኩባንያዎች ድጋፍ በመደረግ ላይ ነው። ድጋፉ እየተደረገ ያለው በጃፓን የኢኮኖሚ፣ ንግድ አና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መሆኑንም ተናግረዋል። የቴክኒክ ድጋፉ በኢትዮጵያ ያሉ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎችን የምርት ጥራት በማሻሻል ወደ ጃፓን ገበያ እንዲገቡ ለማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል። በአውደ ጥናቱ በጃፓን መንግስት የቴክኒክ ድጋፍ የተደረገላቸው የ"ኤም ኤ ኤ" እና "ዲ ቢ ኤሊ" የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች እንቅስቃሴ ለተሞክሮ ቀርቧል። ባለፉት አምስት ዓመታት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ዘርፍ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ከውጭ ንግድና ከሥራ እድል ፈጠራ አንጻር የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲጫወት ቆይቷል። የኢፌዲሪ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረ­የሱስ እንዳሉትም ዘርፉ የተለያዩ የሥራ ዕድሎች፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ በመሆኑ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶት እየተሰራ ነው። ኢትዮጵያን በቀላል የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በአፍሪካ ቀዳሚ አገር የማድረግን ግብ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። የምርትና ምርታማነት አቅም ማነስ፣ ጥራት ያለው ምርት አለመኖር፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት እንዲሁም ምርትን ወደ ወጭ ለመላክ የሚያስችል የብቃት ማረጋገጭ አለማግኘት ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፉ እንከን መሆናቸውን ጠቁመዋል። አውደ ጥናቱ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ካይዘን ኢንስቲትዩት እንዲሁም በጃፓን የኢኮኖሚ፣ ንግድ አና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ትብብር የተዘጋጀ ነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም