የለሙ ተፋሰሶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንድንሆን አድርገውናል -የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ነዋሪዎች

3751

ሰቆጣ ሚያዝያ 25/2010 ባለፉት አመታት በተከናወነ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ የለሙ ተፋሰሶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ፡፡

የብሄረሰብ አስተዳደሩ የ2010 ዓ.ም በህብረተሰብ ተሳትፎ  የበጋ  የተፈጥሮ ሃበት ልማት ስራ የመዝጊያ ስነ ስርአት በድሃና ወረዳ ሽማምዳን ቀበሌ ተከናውኗል።

ወጣት እንደሻው እንዳለውና ጓደኞቹ በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ቲያ ቀበሌ የላፀና ተፋሰስን መሰረት በማድረግ በንብ ማነብ ስራ ተሰማርተዋል፡፡

ካሁን ቀደም ምንም አይነት ስራ ስላልነበረው ይቸገር እንደነበር አስታውሷል፡፡

ባለፉት አመታት በአካባቢያቸው ያሉትን ተራራዎች በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በማልማታቸው  ዛሬ የአካባቢው ልምላሜ ተመልሶ የስራ እድል መፍጠሪያ መሆኑን ተናግሯል፡፡

እሱና ለጓደኞቹም በአካባቢው በንብ ማነብ  ስራ ተሰማርተው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን መብቃታቸውን ገልጿል።

በዘንድሮ አመት ብቻ የሰበሰበውን 742 ኪሎ ግራም ማር ለገበያ አቅርቦ በመሸጥ ባገኘው ገቢ የእለት ገቢውን ከሟሟላት ባለፈ መኖሪያ ቤት መገንባት እንደቻለ ተናግሯል፡፡

በተመሳሳይ በድሃና ወረዳ የሽማምዳን  ቀበሌ  ነዋሪ ወታደር  ባየ   ይስማው  በበኩላቸው ከመከላከያ  ሰራዊት  በክብር  ከተመለሱ  በኋላ  ከሌሎች   ጓደኞቻቸው  ጋር  በመሆን የጋውሳ  ተፋሰስ  ጠረንጴዛ  እርከንን መሰረት  በማድረግ  በሰብል  ልማት  ተሰማርተዋል ፡፡

በተፋሰስ ልማት ተደራጅተው ባለፈው የመኸር ባካሄዱት የእርሻ ስራ ከ15 ኩንታል በላይ የነጭ ሽንኩርት ምርት በግላቸው መሰብሰብ መቻላቸውን  ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም ተጠቃሚነታቸውን አጠናክረው ለማስቀጠል በየአመቱ  ለተከናወነው  የአፈርና ውሃ ጥበቃ  ስራ በንቃት እንደሚሳተፉና ተፋሰሶችንም በባለቤትነት እንደሚጠብቁ  ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ  ሃብት  ልማትና  ጥበቃ  ቡድን  መሪ  አቶ  አስፋው  ታፈረ  በበኩላቸው ከጥር  2 ቅን 2010  ጀምሮ  ለ25   ተከታታይ የስራ ቀናት የልማት ስራው መከናወኑን ገልፀዋል።

በዚሁ የልማት ስራም በ19 ሺህ ሄክታር መሬት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ተከናውኗል፡፡

በዚሁ የልማት ስራ በተለያዩ የልማት ቡድኖች የተደራጁ ከ145 ሺህ በላይ የሕብረተሰብ  ክፍሎች  የተሳተፉ ሲሆን ከ190 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አብራርተዋል።

በልማት ስራው የጋራና የማሳ ላይ እርከን ስራ፣ የእርጥበት ማቆያ ስትራክቸሮችና መሰል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ተከናውነዋል።

ብሄረሰብ  አስተዳደሩ  የተፈጥሮ  ሃብት መመናመን  ችግር  በስፋት  የሚስተዋልበት  አካባቢ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት  ለመፍታት  የተፈጥሮ  ሃብት ስራው  አይነተኛ  አማራጭ  ነው።  ይህም  አካባቢው  የሚታወቅበትን  የማር  ምርት  ለማሳደግ  ከፍተኛ  አስተዋፅኦ እንደለው ገልፀዋል፡፡

የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ  በህብረተሰቡ  እንደ  ባህል  ሆኖ  እንዲቀጥል  በስፋት  ይሰራል  ያሉት  ቡድን  መሪው  የለሙ  ተፋሰሶችን  ከሰውና  ከእንስሳት  ንክኪ  ነፃ   በማድረግ  ህብረተሰቡ በበላይነት ሊጠብቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በበጋ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራው ማጠናቀቂያ ፕሮግራም ላይ የአካባቢው አርሶ አደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።