ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የኪነ ጥበብ ሚና ከፍተኛ ነው

59
አዲስ አበባ የካቲት 11/2012 ( ኢዜአ) በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ያጠነጠነ ሙዚቃዊ ተውኔት ከአዲስ አበባ ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ ወጣቶች በታደሙበት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር ዛሬ ለእይታ በቅቷል። የ40 ደቂቃ የመድረክ ቆይታ ያለው ሙዚቃዊ ተውኔቱ መነሻውን በህገ-ወጥ ደላሎች ሽንገላ ተታለው ኑሯቸውን ለመቀየር በሚፈልጉ ወጣቶች ላይ አድርጓል። ከመነሻ እስከ መድረሻው ወጣቶች የሚደርስባቸውን ሰቆቃ፣ እገታ፣ መሰወር፣ የጉልበት ጫና፣ ገንዘብ ብዝበዛ፣ ወሲባዊ ጥቃትና የሞት አደጋን ያሳያል። ከሙዚቃዊ ቲያትሩ በኋላ በተደረገ ውይይት ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ፣ በቋንቋ ክህሎት ማሳደግ፣ አማራጭ የስራ መስኮችን ማሳየትና በኃይማኖት ተቋማት ግንዛቤ መፍጠር ሊተኮርባቸው እንደሚገባ ተነስቷል። ድርጊቱ በተጎጂዎች ላይ ከሚፈጥረው አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ባሻገር በሚያስከትለው ሕልፈተ- ሕይወት በአገርና በህዝብ ላይ የሚያደርሰው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል። በማህበረሰባዊ ግንዛቤ ፈጠራ ረገድም ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ሚናቸው የጎላ በመሆኑ፤ እውነተኛ ታሪኮችም እየቀረቡ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ተመላክቷል። ወንጀሉን ለመከላከል የመገናኛ ብዙኃን፣ የኃይማኖት ተቋማትና በዋናነት ወጣቶች ድርሻቸው ከፍተኛ መሆኑም ተጠቁሟል። በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፀረ ሕገ-ወጥ ዝውውር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፈቲያ ሰይድ ዓለም አቀፉን ወንጀል ለመከላከል በ2007 ዓ.ም. የሕግ ማዕቀፍ መደንገጉን አስታውሰዋል። ይህም ሆኖ ድርጊቱን ማስቆም ባለመቻሉ፣ ዳግም ጥናት ተደርጎ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍ፣ ወንጀሉን በተጠናከረ መንገድ ለመከላከልና ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ አዋጁ በዚህ ዓመት ተሻሽሎ መውጣቱን ተናግረዋል። በቅርቡ ተሻሽሎ በፀደቀው በዚህ አዋጅ የሞት ፍርድ የተካተተበት ሲሆን ፤ የተሰራው ስራ ከወንጀሉ አሳሳቢነት አንጻር አነስተኛ ቢሆንም እንኳን በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የተሳተፉ ተዋናዮችን ተጠያቂ የማድረግ ተግባራት መጀመራቸውንም ኃላፊዋ ገልጸዋል። ህግ የማስከበር ስርዓቱ በማያወላውል ሁኔታ እንደሚተገበር ገልጸው፤ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባለው ኃላፊነት ምርመራ የማድረግ፣ ክስ የመመስረትና ለፍርድ የማቅረብ ተግባሩን እንደሚወጣ ተናግረዋል። ድርጊቱ ከሌሎች ወንጀሎች በተለየ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለውና ከተራ ዜጋ እስከ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እጃቸው የተነከረበትና ተጎጂዎችም ሳያውቁት በድብቅ የሚሳተፉበት እንደሆነም ጠቁመዋል። በመሆኑም "አዋጁን ገቢራዊ ለማድረግ ተጎጂዎችን ጨምሮ ሁለንተናዊ ቅንጅት ይፈልጋል" ነው ያሉት። ከህግ አስከባሪ ተቋማት በተጨማሪ ዜጎችን ለስደት የሚዳርጉ መንስኤዎችን አጥንቶ ለወጣቶች ስራ መፍጠር እንደሚገባም አመልክተዋል። ለዚህም ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ መገናኛ ብዙሃንና ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ነው የጠቆሙት። ዝግጅቱ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ተከላካይ ግብረ ኃይል ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ከብሔራዊ ቲያአትር ጋር በመተባበር የቀረበ መሆኑ ታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም