የአንበጣ መንጋ ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ነው

75
አዲስ አበባ የካቲት 11/2012 ( ኢዜአ) የአንበጣ መንጋ በጎረቤት አገር ኬንያ ተፈልፍሎ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ መሆኑ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። የአንበጣ መንጋው ከኬንያ በመነሳት በደቡብ ኦሮሚያና በደቡብ ክልል ኦሞ ዞን አካባቢ በመከሰቱ የመከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል። በግብርና ሚኒስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ሳላቶ እንዳሉት ከኬንያ ወደ ኢትዮጵያ እየመጣ ያለው የበረሃ አንበጣ በሦስት መንጋ የተከፋፈለ ነው። የአንበጣ መንጋው ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከል ሚኒስቴሩ ከአጋር አካላት ጋር ሆኖ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። “መንጋውን በአግባቡ መከላከል ካልተቻለ በሰብል፣ በእንስሳት መኖና በዕጽዋት ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው” ብለዋል። ከየመንና ሶማሊያ ብቻ ሲገባ የነበረው የበረሃ አንበጣ በአሁኑ ወቅት አድማሱን በማስፋት ከተለያዩ አጎራባች አገሮች ጭምር እየገባ መሆኑን ገልጸው፤  “ይህም የአገሪቱን የመከላከል አቅም እየተፈታተነው” ነው ብለዋል። በቀጣይም በምስራቅና በደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲሁም የበልግ ዝናብ በሚያገኙ አካባቢዎች አንበጣ የመከሰት ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ትንበያዎች ያመለክታሉ። ያደጉና እንቁላል ለመጣል የደረሰ አንበጣ በብዛት እንዳይራባ አስቀድሞ የመድኃኒት ርጭት መካሄዱን የገለጹት አቶ ዘብዴዎስ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ጉዳት ሳያደርስ ለማጥፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተፈለፈለ ያለ አንበጣ ባይኖርም ከአጎራባች አገሮች የሚገባው ስጋት መሆኑን ተናግረዋል። በአንድ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ላይ የሚከሰተው የአንበጣ መንጋ 35 ሺህ ሰዎች በአንድ ቀን የሚመገቡትን የማጥፋት አቅም አለው። ኢትዮጵያ ለአንበጣ መከላከል እስካሁን 80 ሚሊዮን ብር ያወጣች ሲሆን በቀጣይ የዚህን ሁለት እጥፍ ገንዘብ እንደሚያስፈልጋት ይታመናል። አንዳንድ አገራት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ለመከላከል የሚሆን ገንዘብ በመደገፍ ላይ መሆናችውን ያስታወሱት አቶ ዘብዲዎስ የአሜሪካ መንግስት ለምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከል 8 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል። በመካከለኛው ምስራቅ አገራትና በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የተከሰተው የአንባጣ መንጋ በ25 ዓመት ጊዜ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም