በአማራ ክልል የተከሰተው የአንበጣ መንጋ እንቁላሉን እንዳይጥል ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው

73

የካቲት 11/2012 ( ኢዜአ) በአማራ ክልል ስድስት ዞኖች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ እንቁላሉን በመጣል ጉዳት እንዳያደርስ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሰሎሞን አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት የአንበጣ መንጋው በሰሜን ሸዋ፣ ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር፣ ዋግህምራ፣ ምስራቅ ጎጃም ፣ደቡብና ሰሜን ወሎ፣ ዞኖች ተከስቷል።

ከጥር ወር አጋማሽ ጀምሮ  የተከሰተውና የዕድገት ደረጃውን የጨረሰ የአንበጣ መንጋ ምቹ ሁኔታ ካገኘ እንቁላል እየጣለ በመፈልፈል የተዘራ ሰብልና የእንስሳት መኖን ሊጎዳ እንደሚችል ተናግረዋል።

ዶክተር ሰሎሞን የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል የዞንና የወረዳ የግብርና ባለሙያዎች ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት አንበጣው ባረፈባቸው ቆላማ አካባቢዎች፣ አሸዋማ ቦታዎችና የወንዝ ዳርቻዎች የተጠናከረ አሰሳና ቅኝት እያካሄዱ ይገኛሉ።

እስካሁን በተደረገ ጥረትም የአንበጣ መንጋው እንቁላል ጥሎ እንዳልተገኘ ጠቁመው ሆኖም ግን ከተገኘም ከመፈልፈሉ አስቀድሞ ኬሚካል በመርጨት ለማጥፋት ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

አርሶ አደሩም በበጋ ወቅት እያለማ ባለው የመስኖ ሰብልና የበልግ ቡቃያ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በባህላዊ መንገድ በመከላከልና መረጃ በመስጠት  እንዲተባበር  የቢሮው ምክትል ኃላፊው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ የ016 ቀበሌ አርሶ አደር አህመድ ሐሰን በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል  የአንበጣ መንጋ በአንድ ሄክታር መሬት ያለሙትን የማሽላና ማሾ ሰብል ጉዳት እንዳደረሰባቸው  አመልክተዋል።

ከሳምንት በፊት የአንበጣ መንጋው ዳግም በመከሰቱ በበልግ ቡቃያቸው፣ በመስኖ በሚያለሙት አትክልትና ፍራፍሬ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ እየተከላከሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በዋግ ህምራ ዞን ዳህና ወረዳ የ021 ቀበሌ አርሶ አደር እምወደው ካሴ በበኩላቸው ከሳምንት በፊት ተከስቶ የነበረው አንበጣ  በባህላዊ መንገድ በመከላከል አካባቢውን ለቆ እንዲሄድ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ከመስከረም እስከ ህዳር 2012ዓ.ም. መጨረሻ በምስራቅ አማራ አራት ዞኖች ተከስቶ የነበረው የአንበጣ መንጋው  ከአንድ ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት የተዘራ ሰብል ማጥፋቱን በወቅቱ ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም