የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ፤ ህወሃት ትግል የጀመረበትን የካቲት 11 ለማሰብ ደም በመለገስ አከበረ

56
አዲስ አበባ የካቲት 11/2012 (ኢዜአ) የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ትዴፓ) ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) ትግል የጀመረበትን 45ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ አመራሩና አባላቱ ደም ለገሱ። የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄን ጨምሮ ሌሎችም የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በኢትዮጵያ ደም ባንክ ተገኝተው ደም ለግሰዋል። የፓርቲው አመራሮችና አባላት ደም የለገሱት "ለአንድነት፣ ፍትህና እኩልነት ሲሉ መስዋዕትነት የከፈሉ ታጋዮችን" ለማሰብ መሆኑ ታውቋል። አጋጣሚውን በመጠቀም ወላድ እናቶችና አደጋ የደረሰባቸው ዜጎች በሚለገሰው ደም ህይወታቸው እንዲተርፍ የራሳቸውን አስተዋፆኦ ለማድረግ መሆኑንም ዶክተር አረጋዊ ተናግረዋል። "እለቱን በተለየ ፊሽታና ጭፈራ ማክበሩ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል" ያሉት ዶክተር አረጋዊ "በጎ ተግባር በመፈፀም" ማክበሩ ከውስጣዊ እርካታ ባሻገር ለወገን አለኝታነትን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚና ዋና ጸሀፊ አቶ ጊዶና መድህን በበኩላቸው "መሪዎቻችን ከ45 ዓመታት በፊት ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለልማት የከፈሉትን መስዋእትነት ለማስታወስና ደም ለሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች አጋርነትን ለማሳየት" የደም ልገሳው መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡ " ደም አናፈስም ደም እንሰጣለን " በሚል አላማ መንቀሳቀሳቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ፓርቲው ከትግራይም ሆነ አጠቃላይ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን የተሰለፈ መሆኑን ለማሳየትም የደም ልገሳ መርሃ ግብሩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ በተደረገው የደም ልገሳ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከ30 በላይ አባላቱ የተሳተፉ ሲሆን ሌሎች አባላትና ደጋፊዎቻቸውም በያለበት ተመሳሳይ ተግባር መፈፀማቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም