የሕዳሴው ግድብ ድርድር ብቸኛው መፍትሄ የሶስቱን አገራት ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ መስማማት ነው

95

አዲስ አበባ፤ የካቲት 10/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የሕዳሴ ግድብ ድርድር ብቸኛው አማራጭ የአገራቱን ጥቅም የሚያስጠብቅ ስምምነት ላይ መድረስ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአሜሪካው አቻቸው ማይክል ፖምፒዮ ጋር በአገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች የአገሮቻቸውን አጋርነት መሰረት ያደረገ መግለጫ ዛሬ በሸራተን አዲስ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ሂደትን የተመለከተ ጥያቄ ለሚኒስትሮቹ ቀርቦ መልስ ሰጥተውበታል።

ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው እንዳሉት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውሃ አለቃቀቅ ድርድር ብዙ ሂደቶችን በማለፍ በበርካታ ጉዳዮች የሚያቀራርቡ ነጥቦች ላይ የተደረሰበት መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም ቀጣይ ድርድር የሚፈልጉ ጉዳዮች በመኖራቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ ግብፅና ሱዳን ያላቸው አማራጭ የሶስቱንም አገራት ጥቅም የሚያስጠብቅ ስምምነት ላይ መድረስ ብቻ ነው ብለዋል።

ሶስቱ አገራት ለዓመታት ሲያደርጉት የነበረው ድርድር ስኬታማ የሚሆነው አንዳቸው ከሌላኛቸው  መደማመጥና መረዳዳት ሲችሉ መሆኑንም አቶ ገዱ ተናግረዋል።

ድርድሩ የአገራቱን ጥቅም ባማከለ መልኩ ይቋጫል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ሲሉም ተደምጠዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክል ፖምፒዮ በበኩላቸው በተለይ አሜሪካና የዓለም ባንክ በታዛቢነት በተሳተፉበት ድርድር ሶስቱ አገራት ወደሚያቀራርባቸው ነጥቦች መጥተዋል ብለዋል።

አሜሪካ ከመታዘብ በዘለለ በአገራቱ ላይ የምታደርገው ምንም አይነት ጫና የለም ያሉት ፖምፒዮ በቀጣይ አገራቱ በቀሩት ነጥቦች ላይ ይስማማሉ ብለን እንጠብቃለን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም