የካቲት 11 አብሮነትን በማጠናከር ሊከበር ይገባል … የትግራይ ክልል ብልጽግና ፓርቲ

407

አዲስ አበባ፤ የካቲት 10/2012(ኢዜአ) የትግራይ ህዝብ የየካቲት 11 በዓልን በፕሮፓጋንዳ ሳይጠለሽ ወቅቱ የሚጠይቀውን አብሮነት በማጠናከር ሊያከብረው እንደሚገባ የትግራይ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ገለጸ።

የትግራይ ክልል የብልፅግና ፓርቲ 45ኛውን የየካቲት 11 በዓል በማስመልከት “አኩሪው የትግራይ ህዝብ የጸረ-ጭቆና ተጋድሎና መስዋዕትነት በከሰሩ ሃይሎች አይራከስም፤ የቡድናዊ ፍላጎት መጠቀሚያም አይሆንም” በሚል ርዕስ መግለጫ አውጥቷል።

የመግለጫውን መልዕክት ያስተላለፉት የብልጽግና ፓርቲ የትግራይ ቅርንጫፍ አመራር አባል ዶክተር አብርሀም በላይ ለትግራይ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዶክተር አብርሃም በመግለጫቸው አገሪቱ እየሄደችበት ያለውን የአንድነት፣ የሰላምና የብልጽግና ጉዞ ከግብ ለማድረስ ከሌሎች ወንድማማች ህዝቦች ጋር ከማንኛውም ጊዜ በላይ ተባብሮና ተከባብሮ መኖር ይገባልም ብለዋል።

የትግራይ ህዝብ ከ45 ዓመታት በፊት ይደርስበት የነበረውን ጭቆናና አፈና በመቃወምና ከሌሎች የአገሪቱ ህዝቦች ጋር በመሆን ባደረገው የትጥቅ ትግል ከ29 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ አዲስ የጉዞ ምዕራፍ እንዲከፈት መሰረት ጥሏል።

የትግራይ ህዝብ መስዋዕትነት የከፈለው በተሻለ የነጻነት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ጥማት ሆኖ ሳለ ከብዙ ዓመታት በኋላም አሁንም የትግራይ ህዝብ የተረጋጋ አየር ለመተንፈስ አዳጋች ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ዶክተር አብርሃም በመልዕክታቸው ተናግረዋል።

እርሳቸው እንዳሉት የህዝቡን ትግል በሚያንቋሽሹ ኃይሎችና የህዝቡን ትግል የቡድን ትግል ለማድረግ የሚፈልጉ ኃይሎች ህዝቡ ውጥረት ውስጥ እንዲገባ እያደረጉ ናቸው።

የትግራይ ህዝብ ከውጥረት ወጥቶ ሰላምና ደህንነት እንዲሰማው በተለያዩ ጊዜያት ሆን ተብለው የሚሰነዘሩ ጠብአጫሪ ንግግሮች በአስቸኳይ ሊታረሙና ለወደፊትም ጥንቃቄ ሊደረግባቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዶክተር አብርሃም እንዳሉት በወቅቱ ፖለቲካ በሰከሩ የፖለቲካ፣ የሚዲያና የአክቲቪስት ልሂቃን ሆን ተብለው የሚወረወሩ የጥላቻ ቃላት በቀጣይ አገሪቱን ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍሉ ተናግረዋል።

“በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይም ጥቁር ነጥብ የሚያስቀምጡ በመሆናቸው ለሰላም፣ ለይቅር ባይነትና ለለውጥ የሚታገሉ ኃይሎችም ሆነ ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ድርጊቱን ሊኮንኑት ይገባል” ብለዋል።

አንዳንድ የማህበረሰብ አንቂዎች የተጽዕኖ ፈጣሪነታቸውና የተቀባይነታቸው መሰረት ህዝብ እና የህዝብ ፍላጎት መሆኑን ተገንዝበው በጎ ተግባር ከመፈጸም ይልቅ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ በሚያሰሯጫቸው መልዕክቶች በህዝቦች መካከል መቃቃር በመፍጠር ላይ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ሚዛናዊ ያልሆኑ አንዳንዴም የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት በአገርና በህዝብ ላይ ክህደት ሲፈጽሙ ማየት በአገሪቱ ላይ የተጋረጠ ወቅታዊ አደጋ መሆኑንም አመልክተዋል።

ዶክተር አብርሃም እንዳሉት የህዝብ የነጻነትና የእኩልነት ትግል ለቡድናዊና ለግላዊ ዓላማ ለማዋል የሚደረገው ሙከራ አግባብ አይደለም።

ባለፉት ዓመታት የፖለቲካ መሪዎች ስልጣንን ከህዝብ ማገልገያ መሳሪያነት ወደግልና ቡድናዊ የጥቅም ትስስር መጠቀሚያነት በማዋላቸው ህዝብና አገርን ለኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ኪሳራ ሲዳርጉ ቆይተዋል።

በመሆኑም የየካቲት 11 ክብረ በዓል በፕሮፖጋንዳ ኃይሎች ሳይጠለሽ እንዲከበር የትግራይ ህዝብ ህዝባዊ ትግሉን ለግልና ቡድናዊ ፍላጎት የሚፈልጉ ኃይሎችን ወደጎን በማለት ወቅቱ የሚጠይቀውን አብሮነት በማጠናከር መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

አገሪቱ እየሄደችበት ያለውን የአንድነት፣ የሰላምና የብዕጽግና ጉዞ ከግብ ለማድረስ ከሌሎች ወንድማማች ህዝቦች ጋር ከማንኛውም ጊዜ በላይ ተባብሮና ተከባብሮ መኖር እንዳለበትም አሳስበዋል።